በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጨፌው የአቶ ታዬ ደንደኣን ያለመከሰስ መብት አነሣ


ጨፌው የአቶ ታዬ ደንደኣን ያለመከሰስ መብት አነሣ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:54 0:00

ጨፌው የአቶ ታዬ ደንደኣን ያለመከሰስ መብት አነሣ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት፣ ከትላንት ጀምሮ ባካሔደው መደበኛ ጉባኤው፣ የቀድሞውን የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ደ’ኤታ የአቶ ታዬ ደንደአን ያለመከሰስ መብት አነሣ።

የአቶ ታዬ ዳንዳአ ያለመከስስ መብት መነሣት እንዳሳዘናቸው፣ ባለቤታቸው ወይዘሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት/ጨፌ ኦሮሚያ/፣ የአቶ ታዬ ዳንደኣን ያለመከስስ መብት ያነሣው፣ ከትላንት እሑድ፣ የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአዳማ ከተማ እያካሔደ ባለው 6ኛ ዓመት 3ኛ የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤው ነው። አቶ ታዬ የተሰጣቸውን የሕዝብ አደራ ወደ ጎን በመተው፣ ሀገር ለማፍረስ እየሠሩ ስለመኾኑ በመጠርጠራቸው ያለመከሰስ መብታቸው እንደተነሳ በምክር ቤቱ ቀርቧል። ውሳኔው በ439 ድጋፍ እና በ14 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ መጽደቁ የክልሉ ብዙኃን መገናኛ ዘግቧል፡፡

ከክልሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ተመርጠው የጨፌ ኦሮሚያ አባል የኾኑት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስተር ደ’ኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፣ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኀይሎች ጋራ በመተሳሰር ለጥፋት ተልእኮ በኅቡእ ሲሠሩ ተደርሶባቸዋል፤” በሚል ተጠርጥረው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ ባለፈው ታኅሣሥ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ነበር፡፡

አቶ ታዬ በፖሊስ ከተያዙ ሁለት ወራት ቢያልፉም፣ እስከ አሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ፣ ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ዛሬ በአቶ ታዬ ደንደኣ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ወይዘሮ ስንታየሁ፣ በውሳኔ ማዘናቸውንም ገልጸዋል።

“በጣም ተሰምቶኛል፤ አሳዝኖኛል። መከሰስ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ከታሰረ በኋላ ሁለት ወር ከዐሥራ አንድ ቀን ቢኾነውም፣ ፍርድ ቤት አልቀረበም። ነገር ግን ዛሬ ያለመከሰስ መብቱ ሲነሣ የተገለጸበት ኹኔታ ያሳዝናል፡፡ ታዬ ራሱን ለሕዝብ ሰጥቶ የሚሠራ እንጂ፣ ራሱን የሚያስቀድም ሰው አይደለም።” ያሉት ወ/ሮ ስንታየሁ “የምክር ቤቱ አባላት ውሳኔውን በነጻነት ስለማስተላለፋቸው እጠራጠራለኹ።” ብለዋል።

ይህን ያሉበትን ምክኒያት ሲያስረዱም፣ “ምክንያቱም ታዬ ራሱ በምክር ቤቱ ስብሰባ እየተሳተፈ የመናገር መብቱን ሲከለከል ነበር፡፡ ሐሳቡን እንዳይገልጽ ድምፅ ማጉያ ይዘጋበት ነበር፡፡ ከምክር ቤቱ የምጠብቀው ፍትሐዊ ውሳኔ ባይኖርም፣ እንደ ሰው አዝኛለኹ።”

በአሁኑ ወቅት አቶ ታዬ በዚያው በሜክሲኮ አካባቢ ባለው የፌደራል ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ወይዘሮ ስንታየሁ ገልጸው፣ ከጠበቃ ጋራ እንዳይገናኙ እንደተከለከሉም ቀደም ሲል ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከጠበቃ ጋራ መገናኘትን እንደማይፈቅድ በሚመለከታቸው ኃላፊዎች እንደተገለጸላቸውም አመልክተዋል። በሚቀጥሉት ቀናት ፍርድ ቤት ከቀረቡ፣ ሒደቱን እየተከታተልን ጠበቃ እንዲቆምላቸው እናደርጋለን፤ በማለትም አክለዋል።

የኦሮሚያ ምክር ቤት በዚሁ መደበኛ ጉባኤው፣ ስለ ክልሉ የሰላም ኹኔታ መነጋገሩን የመንግሥት ብዙኀን መገናኛዎች ዘግበዋል።

በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተዋጊዎች፣ በሰላማዊ መንገድ እንዲገቡ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጉን ያስታወሱት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ “የሕግ ማስከበር ሥራውንም አጠናክሮ ይቀጥላል፤” ብለዋል። ለዚኽም ሕዝቡ እና ጨፌው/ምክር ቤቱ/ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG