የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክልሎች ተወካዮች፣ የሟቾች ቤተሰቦችና የባህር ዳር ከተማ ኗሪዎች፣ በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
«ሰሞኑን ሕይወታቸው ያለፈው የአማራ ክልል መሪዎች፤ በአካባቢያቸው ሳይወሰኑ፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝቦቿ ጥቅም ዕድሜያቸውን ሙሉ የሰጡ፣ አሁን እየተካሄደ ላለውም ለውጥ ዋነኛ ሞተሮች ነበሩ» ሲሉ፣ በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ የተገኙ ጓዶቻቸው ገልጠዋቸዋል፡፡
በዚሁ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ እንደተገለፀው፤ እነዚሁ የአማራ ክልል መሪዎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ተባብረውና ተከባብረው በመስራት የሚያምኑና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስቀድሙ ነበሩም ብለዋቸዋል፡፡
በዚህ፣ የፀጥታ ጥበቃው እጅግ ጥብቅ በነበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ታዳሚዎች፣ ከፍተኛ ኃዘንና ልቅሶ ይታይባቸው እንደነበር ዘጋቢያችን አስቴር ገልጻለች።
በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ የተጠረጠሩትና በፖሊስ የተገደሉት የብርጌዲዬር ጄነራል አሳምነው ፅጌም የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ በዛሬው ቀን በትውልድ ስፍራቸው ላሊበላ መፈፀሙንም፣ አስቴር ጨምራ ዘግባለች።
በሌላም በኩል ሰኔ አስራ አምስት 2011 ዓ.ም በመኖሪያ ቤታቸው እንዳሉ በጠባቂያቸው የተገደሉት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኤታ ማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና በቅርቡ በጡረታ የተሰናበቱትና ለጥየቃ ቤታቸው የነበሩት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ቀብር ዛሬ መቀሌ ከተማ ተፈጽሟል።
በመቀሌ ከተማ የሰማዕታት ሃውልት ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ ነዋሪዎች ስንብት ካደረጉ በኋላ ሥነ ስርዓቱ በጽርሃ ማርያም ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተከናውኗል፡፡
የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ