በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መለስ ዜናዊ ኢህአዴግ ከግምታቸው በላቀ ደረጃ ማሸነፉን ተናገሩ


እስካሁን የተረጋገጠ አንድ ተመራጭ ያላቸው ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ ዛሬ የጠራውን ሰልፍ “ድራማ” ብለውታል

ዛሬ በአዲስ አበባው የመስቀል አደባባይ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ የኢህአዲግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ እና ሌሎች የፓርቲው አመራሮች እና በሺዎች የተቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ተገኝተዋል።

ለተሰብሳቢዎቹ ንግግር ያደረጉት አቶ መለስ ዜናዊ ፓርቲያቸው ከግምታቸው በላቀ ሁኔታ ማሸነፉን ገልጸዋል። ሆኖም በኢህአዴግ የሚመሰረተው መንግስት ድምጽ ያልሰጡትንም ዜጎች በዕኩልነት እንደሚያገለግል ቃል ገብተዋል።

“አገራችንን በሚቀጥሉት አምስት አመታት ሊመራ ይገባል ያለውን ድርጅት በሰፊ አገራዊ መግባባት እንደሰየመ ግልጽ ሆኑል” ብለዋ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መልስ ዜናዊ በአብዮት አደባባይ
ጠቅላይ ሚኒስትር መልስ ዜናዊ በአብዮት አደባባይ

ተቃዋሚዎችም ውጤቱን በጸጋ እንዲቀበሉ አቶ መለስ ጥሪ አቅርበዋል። “የህዝቡን ብይን ሰበብ አስባብ ሳይፈልጉ በጸጋ ቢቀበሉ፣ ህዝቡ ያልወደደላቸው ነገር ምን እንደሆነ በሰከነ አእምሮ አጢነው ለማስተካከል ቆርጠው ቢነሱ፤ ህዝቡ ፍትሃዊ ዳኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስመስክሯልና በሚቀጥለው ጊዜ ውጤታቸውን አይቶ ሊክሳቸው እንደሚችል ሊገነዘቡ ይገባል።” ብለዋል አቶ መለስ።

በተለይ ተቃዋሚዎችን በተመለከተ ሲናገሩ ከዚህ በፊት ካንጸባረቁት አቋም የተለሳለሱ መስለው ታይተዋል። ካሁን ቀደም ለፓርላማው ሲያብራሩ ከምርጫው በኋላ በህግ የሚጠየቁ ተቃዋሚዎች መኖራቸውን መጠቆማቸው ሲታወስ የዛሬ ንግግራቸው ግን ያን የደገመ አልነበረም። ያለፈው አልፏል ሲሉ ነው የተደመጡት።

የአውሮፓ ህብረት ታዛቢ ቡድን መሪ ታይስ በርማን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሰፊ ትርጉም እንዲኖረው የግል ምኞታቸውን ገልጸዋል ። ለተቃዋሚዎች የመጫወቻውን ሜዳ ከማስተካከል አንጻር አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለውም ተስፋ አድርገዋል።

ተቃዋሚዎችም ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተሉ ነው። የኢዴፓው ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው “ማሸነፋቸው ጥርጥር የለውም፤ ጥያቄው እንዴት አሸነፉ ነው?” በማለት መልሰዋል።

በዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ “ድምጻችን ይከበር” የሚሉና በኒውዮርክ መሰረቱን ያደረገው ሂውማን ራይትስ ወች ስለምርጫው የሰጠውን አስተያየት የሚያወግዙ መፈክሮች በስፋት ተደምጠዋል።

XS
SM
MD
LG