እሁድ ግንቦት 15 ቀን 2002 አመት ምህረት የተካሄደውን የሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የ2002ኡ የሀገራዊ ምርጫ በ1997 ከተደረገው ሂደት የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው ምርጫ ውጤቱን ለመቀልበስ በህዝቡ ዘንድ የሚደረግ ምንም አይነት ጸረ-ሰላም ተግባር የለም ያሉት አቶ መልስ፤ ይንን አቛም የወሰዱት ኢህአዴግን የመረጡ ብቻ ሳይሆኑ ለተቃዋሚዎች ድምጻቸውን የሰጡ ዜጎችም ጭምር ናቸው ብለዋል።
ከምርጫው በፊት ተፈጽመዋል ያሉዋቸውን ወንጀሎች መንግስታቸው እየመዘገበ መሆኑን አስቀድመው መናገራቸውን ያስታወሱት አቶ መለስ፤ በዛሬው ንግግራቸውም ይህንኑ አስታውሰዋል።
“ዝርዝሮቹን ዘግበናቸዋል። በሰነድ ይዘናቸዋል። የተሰበሰበው ዶሴ በአሁኑ ሰአት እንዲዘጋ እንዲቆለፍበት ወስነናል።” ብለዋል አቶ መለስ።
ይህንን ያደረጉት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ለማስደሰት ብለው ሳይሆን፤ የመረጣቸው ዜጋ መከበር ስላለበት ነው ብለዋል።
በትናንትናው እለት አቶ መለስ በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ለተቃዋሚዎች ምክር አዘል ጥሪ አድርገው ነበር።
“የህዝቡን ብይን ሰበብ አስባብ ሳይፈልጉ በጸጋ ቢቀበሉ፣ ህዝቡ ያልወደደላቸው ነገር ምን እንደሆነ በሰከነ አእምሮ አጢነው ለማስተካከል ቆርጠው ቢነሱ፤ ህዝቡ ፍትሃዊ ዳኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስመስክሯልና በሚቀጥለው ጊዜ ውጤታቸውን አይቶ ሊክሳቸው እንደሚችል ሊገነዘቡ ይገባል።” ብለዋል አቶ መለስ።
በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የእሁዱ ምርጫ ታዛቢዎቻቸው በሌሉበትና በተዋከቡበት ሁኔታ በመከናወኑ፤ ውጤቱን እንደማይቀበሉትና እንደገና የድምጽ አሰጣጡ እንዲከናውን ጥሪ አድርገዋል።
ምርጫውን የታዘበው የአውሮፓ ህብረት በትናንትናው እለት በሂልተን ሆቴል በሰጠው መግለጫ ምርጫው ከፍተኛ ብዛት ያላቸው መራጮች የተሳተፉበትና ሰላማዊ ቢሆንም እየጠበበ በሄደው የፖለቲካ ምህዳርና እኩልነት በጎደለው የመወዳደርያ ሜዳ መዘፈቁ አልቀርም ሲል አስታውቛል።
አቶ መለስ ዛሬ ለተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ግልጽ መልእክት አስተላልፈዋል።
“ከዚያ አልፎ ምርጫው እንደገና መደገም አለበት እና የመሳሰሉ ምንም አይነት የህግ መሰረት የሌላቸው እርምጃዎችን እንወስዳለን ቢሉ፤ የመንግስትን የሰላም እጅ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡን ጨዋነትና ሰላም ፈላጊነት ረግጠን እንሄዳለን ቢሉ፤ ውጤቱ ለነርሱ የሚያምር የሚሆን አይመስለኝም።” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ።
ሰኞለት የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪን በጽህፈት ቤታቸው ጠርተው ያነጋገሩት አቶ መለስ በቡድኑ ሪፖርት ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።
አል-ጀዚራና አንዳንድ የዜና አውታሮች ምንጮችን ጠቅሰው እንደዘገቡት አቶ መለስ የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢን ወደ ጽህፈት ቤታቸው ሰኞለት ጠርተው፤ ብርቱ ንግግር ተናግረዋቸዋል።
በማግስቱ በመስቀል አደባባይ አቶ መለስ ባደረጉት ንግግር “የውጭ ሀይሎች” ያሏቸው የህዝቡን ይሁንታ ተቀብለው፤ በዚሁ መሰረት ስራቸውን እንዲያከናውኑ በአጽንዖት ተናግረዋል።
(የሬድዮ ዘገባውን በገጹ በስተቀኝ ያገኛሉ)