ዋሽንግተን ዲሲ —
የቀድሞው የላይቤሪያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አጊስቲም ናጋፉና ለ2017ቱ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለመወዳደር እንደሚፈልጉ ትናንት ማክሰኞ ይፋ አደረጉ።
በዚሁ መሠረት፣ ለምዕራብ አፍሪቃዊቷ አገር ፕሬዚደንትነት ከሚወዳደሩት ከወቅቱ ምክትል ፕሬዚደንት ጆሰፍ ቦካይ ከታዋቂው ኳስ ተጫዋችና የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ኰንግሬስ ፓርቲው ጆርጅ ማኔ ዋህ ከ ሊበርቲ ፓርቲው ቻርልስ ብሩምስኪን እና የቀድሞው ፕሬዚደንት ቻርልስ ቴይለር ወዳጅ ከሆኑት ነጋዴ ከበኖኒ ዩረይ ጋር ሊገጥሙ ነው ማለት ነው።
በፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ አስተዳደር የገንዘብ ሚኒስትርም የነበሩት ናጋፉና ለአሜሪካ ድምጽ የአፍሪቃ አገልግሎት በሰጡት ቃል፣ በሕዝብ አስተዳደርም ሆነ በአመራር እረገድ በቂና አኩሪ ልምድ፣ ከጥሩ ስም ጋር ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል።