ከድንበሩ በኢትዮጵያ በኩልም በኬንያ በኩልም የሚኖሩት ኦሮሞዎች በመሆናቸው ኦሮሞ የኦሮሞን ንብረት አይዘርፍም፤ በባሕላችንም የለም፤ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትም ዘራፊ ሠራዊት አይደለም፤ እንዲህ ዓይነት ጥቃቶችን በተደጋጋሚ የሚያደርሱት የኢትዮጵያ ወታደሮች ናቸውየኦሮሞ ነፃነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ
የኢትዮጵያ ወታደሮች ሰሞኑን የኬንያን ድንበር ተሻግረው ሦስት የኬንያን ፖሊሶች በደፈጣ መግደል የሚናገሩ ዘገባዎች በኬንያ ጋዜጦች መውጣታቸው ይታወሣል፡፡
እኛም ጉዳዩን ለማጣራት እያደረግን ባለነው ጥረት ትናንት ያነጋገርናቸው የኬንያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ቻርልስ ኦዊኖ ደፈጣውን የፈፀሙትና የኬንያ ፖሊሶችን የገደሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ሳይሆኑ የኦሮሞ አማፂያን ናቸው፤ የተገደሉትም መኮንኖች ሁለት ናቸው ብለውናል፡፡
ስለጉዳዩ መግለጫ የሰጡን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ የኬንያን ፖሊስ ውንጀላ አስተባብለዋል፡፡
“ከድንበሩ በኢትዮጵያ በኩልም በኬንያ በኩልም የሚኖሩት ኦሮሞዎች በመሆናቸው ኦሮሞ የኦሮሞን ንብረት አይዘርፍም፤ በባሕላችንም የለም፤ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትም ዘራፊ ሠራዊት አይደለም፤ እንዲህ ዓይነት ጥቃቶችን በተደጋጋሚ የሚያደርሱት የኢትዮጵያ ወታደሮች ናቸው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያሉ የወሰን ኬላዎች መዘጋታቸውንና አለመዘጋታቸውን በሚመለከት የሚጋጩ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
ስታንዳርድ የሚባለው የኬንያ ጋዜጣ ሞያሌ፣ ሶሎሎ፣ ፎሮሌ፣ ዱካናና ኢሌሬት ላይ ያሉ መተላለፊያ ኬላዎች መዘጋታቸውን ነዋሪዎች እንደነገሩት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የቪኦኤ ኦሮምኛ ዝግጅት ክፍል ካነጋገራቸው የመርሳቢት ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አባ ዲዳ “በአካባቢው ሰው ስለተገደለ ሕዝቡ በፍራቻ ከቦታ ቦታ መንቀሣቀስ አቁሟል፤ የኢትዮጵያን ባላውቅም በኬንያ በኩል ግን ማንም ድንበር እንዳይሻገር ተብሎ አልተነገረም” ብለዋል፡፡
ኬንያ ውስጥ ማንም ኢትዮጵያዊ አማፂ ኃይል እንደማይንቀሳቀስ የገለፁት የኬንያ ፖሊስ ቃልአቀባይ “በኢትዮጵያም በኬንያም በአካባቢው የሠፈሩት የቦረና ጎሣ አባላት በመሆናቸው እንቅስቃሴአቸውን ማቆምና መቆጣጠር አይቻልም” ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መንግሥት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ማግኘት አልቻልንም፤ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያና ኬንያ ተፈላጊዎችን አሳልፎ የመሰጣጠት፣ የአካባቢውን ደኅንነት በጋራ የመጠበቅ ስምምነትና እንቅስቃሴ እንዳላቸው የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ቀደም ሲል ለቪኦኤ ገልፀው የሰሞኑን አጋጣሚ አስመልክቶ “… በጋዜጣ ስለተዘገበ ብቻ እውነት ነው ማለት አይደለም…” ብለዋል፡፡
ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡