በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኬንያ ፖሊስ መኮንኖች ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ተገደሉ


የኬንያ ፖሊስ
የኬንያ ፖሊስ

“የኢትዮጵያ ወታደሮች የኬንያን ድንበር ዘልቀው ሦስት የኬንያ ፖሊሶችን ገደሉ” ሲሉ የኬንያ ጋዜጦች ፅፈዋል፤ የሃገሪቱ ፖሊስ ግን ሰዎቹን የገደሉት የኢትዮጵያ ታጣቂ አማፂያን እንጂ የመንግሥቱ ወታደሮች አይደሉም ይላል፡፡

“ናይሮቢ በኢትዮጵያ ወታደሮች ስለተገደሉ ሦስት የኬንያ ፖሊስ መኮንኖች ከአዲስ አበባ ማብራሪያ ልትጠይቅ ነው” ሲሉ የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

ሜል ኤንድ ጋርዲያን አፍሪካ የሚባለው የዜና አውታር ባወጣው ዘገባ “ኢትዮጵያ ወታደሮቿ የኬንያን ድንበር ዘልቀው ገብተው መርሳቢት አካባቢ ወታደሮቿን ከገደሉ በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ የመግባት አደጋ ተደቅኖባታል” ሲል ፅፏል፡፡

ይህንኑ ባለፈው ዓርብ ተፈፀመ የተባለውን ድንበር ዘለል ጥቃት ተከትሎም ኬንያ ወታደሮቿን ጨምሮ የፀጥታ ኃይሎቿን በአካባቢው ማሠማራቷን በኬንያ በሥርጭት ግዝፈቱ ቀዳሚ የሆነው የዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ፣ የትናንት ዕሁድ ዕትም “ሰንዴይ ኔሽን” ዘግቧል፡፡

ዘገባው የኢትዮጵያ ወታደሮች የኬንያን ድንበር ዘልቀው ደፈጣ ካደረጉ በኋላ ተሽከርካሪያቸውን አቃጥለው አ4ራት ብረት እንደወሰድ ይናገራል፡፡

የመርሳቤት አውራጃ ፖሊስ ኮሚሽነር ሞፋት ካንጊ ለሰንዴይ ኔሽን በሰጡት ቃል እንዲህ ዓይነት ድንበር ዘለል ጉዳዮች የሚያዙት በዲፕሎማሲ ደረጃ መሆኑን ገልፀው ሁኔታው ለምን እንደተፈጠረ ከኢትዮጵያ ማብራሪያ እንደሚጠይቁ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡

“እኛ የእነርሱን ግዛት ደፍረን አናውቅም፤ ለምን ፖሊሶቻችን ላይ ጥቃት እንዳደረሱ ማወቅ እንፈልጋለን” ብለዋል የአውራጃው ፖሊስ ኮሚሽነር ሞፋት ካንጊ፡፡

የኢትዮጵያ ወታደሮች ኬንያ የገቡ ታጣቂዎችን ሲያሳድዱ እንደነበር የተዘገበ ሲሆን ከኢትዮጵያ አንዳችም ማስጠንቀቂያ እንዳልደረሣቸው የአውራጃው ኮሚሽነር መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡

የኬንያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ቻርልስ ኦዊኖ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ግን ጥቃቱን የፈፀሙት የኢትዮጵያ ወታደሮች ሳይሆኑ የኦሮሞ አማፂያን ናቸው፤ የተገደሉት የፖሊስ መኮንኖችም ቁጥር ሦስት ሳይሆን ሁለት ናቸው” ብለዋል፡፡

ጥቃት አድራሾቹ ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባታቸውንና ማንንም አለማሠራቸውን ቃል አቀባዩ ኦዌን ተናግረው ጥፋተኞቹን ለማደን ከኢትዮጵያ ጋር በዲፕሎማሲ መንገድ እየሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል በሁለቱ ሃገሮች መካከል የጋራ ፀጥታን ለማስከበር የጋራ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ እና ተፈላጊዎችን አሣልፎ ለመሰጣጠት ስምምነት መኖሩን አመልክተዋል፡፡

“ቀደም ሲል ኢሲኦሎ በሚባለው አካባቢ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር ይደበቅ ነበር፤ አሁን ግን ሁለቱም ወገኖች አብረው እየሠሩ በመሆናቸው ችግሩ የለም፡፡ አሁን እንደድሮው ጥቃት አድርሰው መደበቅ አይችሉም” ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኦነግን ቃል አቀባይ ኦቦ ቶሌራ አደባ ነገ፤ ማክሰኞ፤ ኅዳር 14/2008 ዓ.ም መግለጫ እንደሚሰጡን ገልፀውልናል፡፡

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

የኬንያ ፖሊስ መኮንኖች ኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ተገደሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:04 0:00

XS
SM
MD
LG