የእሥላማዊ ሪፐሊካችን ጠላቶች ሁከት አዘል ፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎችን እያራገቡ ነው ሲሉ የኢራን የበላይ መሪ አያቶላ አሊ ሃሜኒ ዛሬ ክሥ አሰምተዋል።
ባለፈው ሣምንት ለተጫረው ተቃውሞ የኢራን ጠላቶች ያሏቸው ወገኖች “በሃገራችን ላይ ችግሮችን ለመፍጠር ገንዘብ፣ የጦር መሣሪያ፣ የፖለቲካና የስለላን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እየተጠቀሙ ነው” ብለዋል።
ለስድስተኛ ቀን በቀጠለው የኢራን የተቃውሞ ንቅናቄ ውስጥ በነበሩት ግጭቶች ባለፈው ሌሊት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውንና ተቃውሞው ከተቀጣጠለ አንስቶ የተገደለው ሰው ቁጥር ከሃያ መብለጡን የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ዛሬ ዘግቧል።
ተቃውሞዎቹ የተጫሩትና አልበርድ ያሉት ኢራን ውስጥ ያሉ የምጣኔ ኃብት ሁኔታዎች በሕዝቡ ውስጥ ባስነሱት ቅሬታ መሆኑ ይሰማል።
የሌሊቱ ተቃውሞና ግጭቶች የተፈጠሩት “በሁከተኞችና በሕገወጦች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ” ሲሉ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ ካስጠነቀቁ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።
በተቃውሞ ሰልፎቹ ሳቢያ በሣምንቱ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግን በመካከለኛው ምሥራቅ የተፅዕኖ የበላይነትን ለመቆጣጠር በተያዘው ትንቅንቅ የኢራን ጦር ሶሪያ፣ ኢራቅና የመን ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ በሰጡት መግለጫ ባለፉ ጥቂት ቀናት ውስጥ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ አስጊ ቢመስልም እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
"...ገንዘብ፣ ዳቦና ውኃ አጣን ብለው የወጡ ብቻ አይደሉም። ሌሎችም ጥያቄዎች ያሏቸው አሉ፤ ለምሣሌ ለቀቅ ያለ ነፃነትን ይጠይቃሉ..."
“ችግሩ ምን እንደሆነ ማየት ይገባናል፤ ሁሉም ባይሆኑም ተቃውሞውን ለማሰማት አደባባይ የወጣው ሁሉ ከሌሎች ሃገሮች መመሪያ የተቀበለ ነው ማለት እንችልም። በርግጥ እንደዚያ ዓይነቶች ጥቂቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሌሎች ግን በስሜት ተገፋፍውና በእውኑም በኑሯቸው ምክንያት የተሰለፉ አሉ” ብለዋል ሩሃኒ።
ችግሮቻቸው የምጣኔ ኃብት ብቻ እንዳልሆኑም ጠቁመዋል ፕሬዚዳንቱ፤ ገንዘብ፣ ዳቦና ውኃ አጣን ብለው የወጡ ብቻ አይደሉም። ሌሎችም ጥያቄዎች ያሏቸው አሉ፤ ለምሣሌ ለቀቅ ያለ ነፃነትን ይጠይቃሉ። በርግጥ ኢኮኖሚ አንዱ ቢሆንም ሁሉም ጥያቄ ገንዘብና ኢኮኖሚ አይደለም” ብለዋል።
ሩሃኒ ለፓርላማቸው ባደረጉት ንግግር ዩናይትድ ስቴትስን፣ እሥራኤልና በተለይ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያን ኢራን ውስጥ ሁከትን በማቀጣጠልና በማባባስ ከስሰዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ግን የኢራኑን መሪ ንግግር ትናንት ባወጡት የአዲስ ዓመት የትዊተር መልዕክት ሲያጣጥሉ ኢራን ውስጥ “ለውጥ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው” ብለዋል።
“ወቀሳ ወይም ትችትና ተቃውሞ ሥጋት ብቻ ሳይሆኑ ዕድልም ናቸው” ብለዋል በሌላ በኩል ንቅናቄውን ቀለል አድርገው ለማሳየት የሞከሩት የኢራን ፕሬዚዳንት ሩሃኒ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ