በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ማሰሯን ሲፒጄ አስታወቀ


ኢትዮጵያ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ማሰሯን ሲፒጄ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:56 0:00

ኢትዮጵያ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ማሰሯን ሲፒጄ አስታወቀ

በድጋሚ የታደሰ

በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባዔን ለመዘገብ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው የአፍሪካ ኢንተለጀንስ ድረ ገጽ ዘጋቢ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ሐሙስ የካቲት 14፣ 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉን ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) አስታወቀ።

ጋሊንዶ አዲስ አበባ በሚገኘው ስካይ ላይት ሆቴል ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለው፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ከሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ ጋራ ቃለ መጠይቅ እያደረገ በነበረበት ወቅት ሲሆን፣ አቶ በቴም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሲፒጄ ጨምሮ ገልጿል።

የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ አቶ በቴ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በእስሩ ዙሪያ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

ጋሊንዶ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው ከአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በተጨማሪ፣ በተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ዘገባ ለመሥራት መሆኑን እና ኢትዮጵያ ውስጥ መዘገብ የሚያስችለው የጋዜጠኝነት ቪዛ መያዙን፣ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን አስፈላጊውን ፈቃድ ማግኘቱን የሚሠራበት የሚዲያ ተቋም እስሩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። እስሩ ኢ-ፍትሃዊ እንደሆነ በመግለፅም፣ ዘጋቢው በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል።

ጋሊንዶ እና በቴ ሐሙስ እለት የሲቪል ልብስ በለበሱ የደኅንነት አባላት መወሰዳቸውን ያመለከቱት የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም ክፍል ኃላፊ አንጀላ ኩዊንታል፣ ቅዳሜ፣ የካቲት 16፣ 2016 ዓ.ም እለት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ምድብ ችሎት መቅረባቸውን እና "ከሁለት ታጣቂ ቡድኖች ጋራ በመዲናዋ አመፅ ለመቀስቀስ በማሴር" መጠርጠራቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

"ፖሊስ ስልኩን ለመመርመር ጊዜ ስለሚያስልፈገው የሁለት ሳምንት የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ነበር" ያሉት አንጀላ፣ ሆኖም ዳኛው የአንድ ሳምንት ጊዜ መስጠታቸውን እና በመጪው አርብ የካቲት 22 በድጋሚ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አስረድተዋል።

ተጨማሪ ጊዜ የተሰጠው የጋዜጠኛውን ስልክ ከመመርመር በተጨማሪ “ሌሎች ተባባሪ አካላት ካሉ” በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚል ነው።

ጋሊንዶ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለሚሠራበት የሚዲያ ተቋም ደውሎ ስለሁኔታው ማሳወቅ እንደቻለ ያመለከቱት ኩዊንታል፣ ተቋሙ የመደበለት ጠበቃ በአካል እንዳገኘው እና ባለበት የአስም በሽታ ምክንያት ለጤንነቱ ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል።

ሲፒጄ ያለፈውን የአውሮፓውያን 2023 ዓ/ም በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፣ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ስምንት ጋዜጠኞችን በማሠር፣ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ጦርነት የፕሬስ ነፃነትን ይበልጥ አዳክሟል
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:14 0:00

አሁን በቁጥጥር ስር ካሉት ስምንት ጋዜጠኞች ውስጥ አራቱ፣ ካለፈው አመት ሐምሌ ወር ጀምሮ በሥራ ላይ ባለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን እና እስካሁንም ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ያመለከቱት ኩዊንታል፣ ጋሊንዶን ጨምሮ ሁሉም ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ኢንተለጀንስ ድረ ገፅ፣ የምስራቅ አፍሪካ ክፍል ኃላፊ የሆነው የ36 ዓመቱ ጋዜጠኛ ጋሊንዶ፣ እ.አ.አ ከ2013 -2017 ኢትዮጵያ ውስጥ በጋዜጠኝነት ይሠራ ነበር።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተወሰኑ የውጭ ዜግነት ያላቸው ጋዜጠኞች ከኢትዮጵያ የተባረሩ ወይም ሥስራ ፍቃዳቸው የተነጠቀ ቢሆንም ለመጨረሻ ጊዜ ለእስር የተዳረጉት ግን እ.አ.አ በ2011 ዓ.ም የታሰሩት ሁለት የስዊድን ጋዜጠኖች ነበሩ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG