በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራ ጋዜጠኞችን በማሠር ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች - ሲፒጄ


አስራ ስድስት ጋዜጠኞችን በማሠር ኤርትራ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ እንደምትይዝ በጋዜጠኞች መብት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ሲፒጄ ያለፈውን የፈረንጆቹ 2023 ዓ/ም በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

አሥራ ስድስት ጋዜጠኞችን አሥራ የያዘችው ኤርትራ፣ በዓለም 7ኛ ደረጃን እንደምትይዝም ታውቋል። አንዳንዶቹ ጋዜጠኞች በዓለም ለረጅም ግዜ የታሠሩ እንደሆነም ሪፖርቱ አመልክቷል። በሁሉም ጋዜጠኞች ላይ ክስ ተከፍቶ እንደማያውቅም ሪፖርቱ ጠቁሟል።

እስካለፈው ወር ድረስ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የታሠሩት ጋዜጠኞች ቁጥር 47 እንደነበር ያመለከተው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ስምንት ጋዜጠኞችን በማሠር፣ ካሜሩን ደግሞ ስድስት በማሠር የሁለተኛና እና ሶስተኛ ረድፍ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

በኢትዮጵያ በእሥር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኖች ቁጥር፣ በአገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የሚገኙበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያስያል ሲል ሲፒጄ በሪፖርቱ አመልክቷል።

ባለፈው ዓመት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ያስቆመ የሠላም ስምምነት ቢፈረምም፣ በአማራ ክልል በአካባቢው በሚገኙ ኃይሎች እና በፌዴራሉ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት አሁንም እንደቀጠለ ነው ያለው ሲፒጄ፣ ስምንቱም ጋዜጠኞች የታሠሩት ግጭቱን በተመለከተ ዘገባ ካወጡ በኋላ መሆኑን አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም የታሠሩ ጋዜጠኞች ቁጥር እስከአሁን ከታዩት ከፍተኛ ሆኑ ከተመዘገበው ዓመት ጋር እንደሚቀራረብ ያመለከተው ሲፒጄ፣ የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ባለፈው ጥቅምት መጀመሩን ተከትሎ፣ እስራኤል ጋዜጠኞችን በብዛት ካሰሩ አገራት ጎራ መቀላቀሏን አስታውቋል።

ቻይና 44 ጋዜጠኞችን በማሠር ቀዳሚውን ሥፍራ ስትይዝ፣ ሚያንማር 43 በማሠር እንዲሁም፣ ቤላሩስ 28 ጋዜጠኞችን በማሠር የሁለተኛ እና ሶስተኛ ሥፍራን ይዘዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG