በቁጥጥር ሥር የዋሉት ዘጠኝ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች የተያዙት ከስድስት ወር እስከ ሦስት ዓመት በእሥራት ሊያስቀጣ በሚችል ጥፋት ነው ሲሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ዘይኑ ጀማል ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሠራተኞቹ የመብት ጥያቄ “አግባብ አይደለም” እንዳልተባለ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጄነራል ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀው ያቀረቡት የአንድ ሺህ ከመቶ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ አቀራረብ ግን ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ሠራተኞቹና በአሠሪያቸው ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ በድርድር ለመፍታት ጥረት መደረጉንና ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም ለችግሩ የመግባባት መፍትኄ ለማስገኘት ጣልቃ ገብቶ ማደራደሩን ኮሚሽነር አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ በእርሣቸው አባባል “የተወሰኑ የእንቅስቃሴው መሪዎች” ሠራተኛው አድማ እንዲመታ በማስተባበር መቀጠላቸውን ጠቅሰው “የኢትዮጵያን አየርም ሆነ የአየር መንገዱን ዝና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ መልዕክቶችን ለዓለምአቀፍ ድርጅቶች ሲያሠራጩ ቆይተዋል” ብለዋል።
የሠራተኞቹ ጥያቄ በአመዛኙ ከደመወዝ ጋር የተያያዘ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነር ዘይኑ አድራጎቱን የሚያዩት ከሃገር ደኅንነት ጋር አያይዘው መሆኑንም ገልፀው ጉዳዩ ከእንግዲህ የሚታየው በፍርድ ቤት እንደሚሆን አመልክተዋል።
ባለፈው ሣምንት አድማ ከመቱት ሠራተኞች መካከልም በባለሥልጣኑ ዳይሬክተር ጄነራልና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ አባባል “ብዙዎቹ ጥፋታቸውን አምነው ወደ ሥራ ለመመለስ ወስነው እየተመለሱም እንደነበርና አሁን በቁጥጥር ሥር በዋሉት መሪዎቻቸው ግን የተለያዩ ማስፈራሪያዎችና ቅስቀሳዎች እየተካሄዱባቸው እንደነበረ” አመልክተዋል።
ለጥያቄዎቻቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መልስ ካልተሠጣቸው “የሚወድዱትን ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ እንደሚገደዱ” ካስታወቁት ሠራተኞች መካከል የተወሰኑትን አግኝተን ሃሣባቸውን እንዲያሳውቁ፣ ጥያቄዎቻቸው በዝርዝር ምን እንደሆኑና ስለአካሄዳቸውም እንዲናገሩ ጥረት ብናደርግም ለመናገር ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ከአቶ ዘይኑ ጀማል እና ከሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጄነራል ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ጋር ያደረግናቸውን ቃለ-ምልልሶች ከተያያዙት የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ