በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"በጣም አዝነናል፤ ድርጊቱንም እናወግዛለን”- ሲፒጄ


የምሥጋና ቀን በተመስገን ደሣለኝ ቤተሰቦች ቤት - መጋቢት 16/2010 ዓ.ም፤ ጃሞ-አዲስ አበባ
የምሥጋና ቀን በተመስገን ደሣለኝ ቤተሰቦች ቤት - መጋቢት 16/2010 ዓ.ም፤ ጃሞ-አዲስ አበባ

የሰብዓዊ መብቶችና የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ድርጅቶች ግንባር ገጥመው ወይም ኃይሎቻቸውን አስተባብረው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እያደረጉ ያሉት ነገር ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እንዲገነዘቡት ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ድምፆቻቸውን ማሰማት እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ደህንነት ተሟጋች ቡድን (ሲፒጄ) አሳሰበ።

"በጣም አዝነናል፤ ድርጊቱንም እናወግዛለን”- ሲፒጄ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:48 0:00

በቅርብ ግዜ ከእስር የተፈቱትን እስክንድር ነጋን፣ አንዷለም አራጌንና ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ ዐሥራ አንድ ሰዎች ከእሁድ ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ስድስት ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ላይ አምደኞች መሆቻቸውን ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ደህንነት ተሟጋች ቡድን (ሲፒጄ) አስታውቋል። የድርጅቱን የአፍሪካ ቀንድ ተከራካሪ አንጄላ ኲንታልን የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ጠንካራ ጋዜጠኞችና ጸሐፊዎችን ልታፍንበት አይገባም ብለዋል።

“እኛ እስከምናውቀው እስከአሁን ቢያንስ ስድስት ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ላይ አምደኞች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ከታሰሩት መካከል ይገኛሉ። በዚህም እኛ በግልፅ በጣም አዝነናል፤ ድርጊቱንም እናወግዛለን።”

ጉዳዩን የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ከዚህ ቀደም ተቀባይነት በሌለው መልኩ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችንና ጸሐፍያንን በድጋሚ ማሰሩ ነው ይላሉ አንጄላ ኲንታል

“በመጀመሪያ እሥረኞቹን በምን ወንጀል እንደከሰሷቸው በግልፅ እንዲያሳውቁ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጥሪ እናቀርባለን። ጥፋታቸው ምን እንደሆነ እንኳን በግልፅ የሰማነው ነገር እስከአሁን የለም። የእኛ ሥጋት እነርሱን አሥሮ ለማስቀመጥ እንደሰበብ እየተጠቀሙበት ያሉትን ምክንያት ነው አሁን እየተናገሩ ያሉት። ማንም ከቁብ ሊቆጥረው የሚችል አንዳችም የረባ ክሥ አልተመሠረተባቸውም።”

የጋዜጠኞች ደህንነት ተሟጋች ቡድን (ሲፒጄ)የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አሁኑኑ እስረኞቹን እንዲለቅ ጠይቋል። ከታሰሩት ዐሥራ አንድ ሰዎች መካከል እስክንደር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ዘላላም ወርቃገኘሁ፣ በፍቃዱ ሀይሉ፣ማህሌት ፋንታሁና ይድነቃቸው አዲስ ጋዜጠኞችና የኢንተርኔት ላይ አምደኖች መሆናቸውን አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥም በጣም በቅርቡ ከእስር የተፈታውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሁሉም ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ ታስረው የተፈቱ ናቸው።

በተጨማሪም እንዲሁ በቅርቡ የተፈታው የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው አቶ አንዷለም አራጌን ጨምሮ ወይንሸት ሞላ፣አዲሱ ጌትነት፣ስንታየሁ ቸኮልና ተፈራ ተስፋዬም አበረው ታስረው ይገኛሉ።

የድርጅቱን የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ አንጄላ ኲንታልን፤ ከዚህ ቀደም ከመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ወይም ከሚኒስትሩ ከራሳቸው መረጃን እንደሚያገኙ ገልፀው አሁን ግን እምብዛም የሚያረካ ነገር እንዳላገኙ ይናገራሉ።

“ላገኛቸው ትናንት ሞክሬ ነበር፤ እንደገናም እሞክራለሁ። ኮማንድ ፖስቱንም አግኝተን የሆነ ሰው ለማነጋገር እንጥራለን። ነገር ግን የሰብዓዊ መብቶችና የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ድርጅቶች ግንባር ገጥመው ወይም ኃይሎቻቸውን አስተባብረው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እያደረጉ ያሉት ነገር ጨርሶ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እንዲገነዘቡት ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ድምፆቻቸውን ማሰማት አለባቸው። እናም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ጋዜጠኞችንና ሌሎችንም ለማዋከብና ለማንገላታት እንደመሣሪያ መጠቀም ጨርሶ ተቀባይነት ያለው አድራጎት አይደለም።”

ከታሳሪ ቤተሰቦች ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው እስረኞቹ ዛሬ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጎተራ ፔፕሲ እየተባለ በሚጠራው የማኅበረሰብ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ እንደሚገኙ ገልፀውልናል።

በትናንትናው ዕለት እስረኞቹን የጎበኙ ወዳጆቻቸው ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለፁት በዚህ ፖሊስ ጣቢያ በተለይ ወንዶቹ ታሳሪዎች በሚገኙበት ክፍል ከሰበታ አካባቢ ታፍሰው የገቡ ወደ 80 የሚጠጉ እስረኞች እንደሚገኙ ነው።

በሌላ በኩል በኮማንድ ፖስቱ ሥር መታሥሰራቸ የተገለፀው የአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ግቢ መምሕሩና የኢንተርኔት አምደኛው ስዩም ተሾመ እንዲሁም የኦሮምያ ፍትህ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ በማዕከላዊ እንደሚገኙና እስካሁን ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ቤተሰቦቻቸው ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በባሕርዳር ከተማ ውስጥ በአንድ ላይ የነበሩ የዩኒቨርስቲ ምሑራን፣ የመንግሥትና የግል ጋዜጠኞችና ሌሎች ባለሞያዎች በአጠቃላይ 19 ሰዎች ከቅዳሜ መጋቢት 15/2010 ዓ/ም በባሕርዳር ከተማ መታሰራቸውን ወዳጆቻቸውን ጠቅሰን በትናንትናው ምሽት መዘገባችን ይታወሳል።

“ከእስር የተለቀቁ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመልሰው መታሰር በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሥርዓት ለውጥ መሆኑን ማሳያ ነው” ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለፁን በትናንትናው ምሽት መዘገባችን ይታወሳል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG