የኦሊምፒክ ማራቶን የብር ሜዳልያ አሸናፊ ፈይሳ ባለቤቱና እና ሁለት ልጆቹ ዩናይትድ ስቴትስ ገብተዋል።
አትሌቱ ከባለቤቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር መገናኘቱ እንዳስደሰተውም ለአሜሪካ ድምጽ ተናግሯል። የኢትዮጵያ መንግሥት አትሌቱ ወደ ሀገሩ የመመለስ መብቱን የሚያግዱ ነገሮች የሉም ቢልም፤ አትሌቱና ቤተሰቡ ግን ለዚህ የኦሊምፒክ ብሄራዊ ጀግና ዋስትና ስጋት እንዳላቸው በመግለጽ፤ ባለበት ለመቆየት ወስነዋል።
በሪዮ ኦሎምፒክ የብር መዳሊያ አሸናፊው የ27 ዓመቱ አትሌት ፈይሳ ለሊሳ ባለቤት ወ/ሮ ኢፍቱ ሙሊሳ፣ የአምስት ዓመት ሴት ልጁ ሰኮ ፈይሳና የሦስት ዓመት ወንድ ልጁ ሶራ ፈይሳ በትናንትናው ዕለት ዩናይትድ ስቴትስ ሚያሚ አየር ማረፊያ ሲገቡ አትሌዩ ተገኝቶ ተቀብሏቸዋል። በአሁኑ ሰዓትም በአሪዞና ግዛት በፍላግስታፍ ከተማ ይገኛል።
አትሌት ያደገውና የኖረው ብዙ ሰዎች ባሉበት ቤት ውስጥ በመሆኑ ለብቻው ሲሆን ኑሮ በጣም ከብዶት እንደነበር ለአሜሪካ ድምጽ ተናግሯል። አሁን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው የተለየ ችሎታ ላላቸው ሰዎች በሚሰጥ ልዩ የስደተኛ ቪዛ ሲሆን ቤተሰቦቹም ሊመጡ የቻሉት በዚሁ መሰረት በተመቻቸው የቪዛ ሥርዓት መሆኑን ተናግሯል። አትሌት ፈይሳ ከወራት በፊት ለአሜሪካ ድምጽ በሰጠው ቃለምልልስ ከቤተሰቦቹ መለየቱ ከባድ መሆኑን እነርሱ ግን በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልፆ ነበር።
ሌሊሳ ወደ ሀገሩ ቢመለስ ሊታሰር እንደሚችል ስጋት እንዳለው ገለፆ ወደ ኢትዮጵያ እንደማይመለስ ካስታወቀ በኋላ ባለቤቱ ወ/ሮ ኢፍቱ ሙሊሳ ሌሊሳ ባደረገው ነገር እንዳልተገረመች፤ “በማህበረሰብ የመገናኛ ብዙሃን የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ሲመለከት፤ ውስጡ ይቃጠል ነበር። ሰዎች ሲደበደቡና ሲታሰሩ ሲመለከት እርር ድብን ይል ነበር። ስለዚህ ያደረገውን ስመለከት ብዙም እንግዳ ነገር አልሆነብኝም፣ አልደነቀኝም። ምክንያቱም ውስጥ ውስጡን በሁኔታዎች ቁጣ ነበረበት” ብላ ነበር።
ፈይሳ አሁን ከቤተሰቦቹ ጋር ተገናኝቷል። በዚህም በጣም ደስተኛ እንደሆነ ገልጿል። በተለይ ሴት ልጁ ገና አሜሪካን ኢምባሲ ቪዛ ለማግኘት ስትገባና “አሜሪካ” የሚለውን ማስታወቂያ ስታይ “አባቴን አምጡ” ብላ መጠየቅ ጀምራ ነበር ብሏል። አሁን ከብቸኝነት ወጥቶ ተረጋግቶ ልምምዱን እንደሚያደርግም ገልጿል።
በኢትዮጵያ በሕዳር ወር 2008 ዓ.ም በኦሮሚያ የተጀመረው ተቃውሞ ከዛም በአማራ ክልል እንዲሁ በደቡብ ክልል የተወሰኑ ከተሞች ተዛምቶ እንደ ሂዩማን ራይትስ ወችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሉ ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች ባወጡት ሪፖርት፤ የሰብዓዊ መብትና የፖለቲካ ነፃነትን በመጠየቅ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል የሚል ሪፖርት አውጥተዋል በቅርቡም በዚሁ ምክኒያት የታሰር ከ21 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈተዋል።
ፈይሳም በወቅቱ በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን የመብት ጥሰት ተቃውሞ በኦሎምፒክ አደባባይ መውጣቱን ተናግሮ ነበር።
በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ለአትሌት ሌሊሳ ፈይሳ ስኬት ደስታቸውን ከገለጹ በኋላ አትሌቱ ወደ ሀገሩ የመመለስ መብቱን የሚያግዱ ነገሮች እንደሌሉ ተናግረው ነበር፤ አትሌቱና ቤተሰቡ ግን ለዚህ የኦሊምፒክ ብሄራዊ ጀግና ዋስትና ስጋት እንዳላቸው በመግለጽ፤ ባለበት እንዲቆይ ወስነዋል።
በትናንትናው ምሽት ለአሶሺየትድ ፕረስ የዜና አውታር የተናገረው አትሌት “አይምሮየ ያተኮረው በሃገር ቤት ባለው ሁኔታ ነው። በሩጫ ላይም ሆንኩ ስተኛና ጋደም ስል በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታና የቤተሰቤ ጉዳይ በአእምሮየ ይመላለሳል። በሕዝቤ ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ደጋግመው በአይምሮየ ድቅን ይላሉ።” ብሏል።
ፈይሳ በጹሑፍ ባወጣው መግጫ ደግሞ፤ ከቤተሰቦቼ ጋር እንዲገናኝ የረዳውን የአሜሪካ መንግሥት አመስግኖ የዩናይትድ ስቴትስና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ በሚሰጡት ማናቸውም እርዳታ በሀገሪቱ እያዘቀጠ የሄደውን የሰብዓዊ መብት ይዞታ ከግንዛቤ እንዲያስገቡ ተማጽኗል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ