በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ድምጽ አልባው "ድርቅ" በኢትዮጵያ


ሳራ አሊሶ የተባለች እናት የአንድ ወር ልጇን ታቅፋ በሶማሌ ክልል በዋርዴር ዞን በሞላዴ ቀበሌ የምግብና የውሃ ርዳታ እየጠበቀች በጥር/20/2009
ሳራ አሊሶ የተባለች እናት የአንድ ወር ልጇን ታቅፋ በሶማሌ ክልል በዋርዴር ዞን በሞላዴ ቀበሌ የምግብና የውሃ ርዳታ እየጠበቀች በጥር/20/2009

በኢትዮጵያ ድርቅ መከሰቱ በይፋ ከተገለፀ አራት ወራት አስቆጥሯል። እስካሁን የሞተ ሰው ሪፖርት ባይደረግም ድርቁ ግን ከፍተኛ በመሆኑ 7.8 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረት መጋለጡና እንስሳት መጨረሱ ይፋ ተደርጓል። መንግሥት ድርቁን ለመቋቋምና ርዳታውን በአግባቡ ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ “ረሃብ” የለም ይላል። የነገሌ ቦረና ነዋሪ በበኩላቸው“ሌሎች እንዴት እንደሚታያቸው አላውቅም እንጂ እኛ አካባቢ ድርቁም ከፍተኛ ነው ረሀብም አለ” ይላሉ።

በአፍሪካ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ቆላማ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ካጋጠመው ሁሉ የከፋ ድርቅ በዚህ ዓመት ተከስቷል። እንደ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ባሉ ሀገሮች ጦርነት እና ግጭት ሁኔታውን አባብሶ “ረሀብ” ገብቷል። ከምግብ እጥረቱ በተጨማሪ በውሃ እጥረትና በበሽታ ሰዎች መሞት ጀምረዋል።

ድምጽ አልባው "ድርቅ" በኢትዮጵያ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:33 0:00

በኢትዮጵያ ድርቅ እንጂ “ረሀብ” አልተከሰተም ተብሏል። ከእንስሳት ሞት እና በምግብ እጥረት ከተጎዱ ሰዎች ውጭ እስካሁን የሰው ሞት ሪፖርት አልተደረገም። የኢትዮጵያ መንግሥትና የለጋሽ ድርጅት አጋሮቹ የመኸር ቅድም አዝመራ ምርመራ ማድረጋቸውን ገልፀው በታኅሣሥ ወር ይፋ ባደረጉት የሰብዓዊ መጠየቂያ ሰነድ (Humanitarian Requirements Document- HRD) መሰረት በኦሮሚያ በቦረናና በጉጂ ዞኖች፣ በባሌ ዞን እና በምስራቅ ሐረርጌ፣ በሶማሌ ክልል፣ በደቡብ፣ በአፋር እና በአማራ ክልል በአጠቃላይ 5.6 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልግ ይፋ አድርገው ነበር።

በሶማሌ ክልል በዋርዴር ወረዳ በድርቁ የተጎዱ ሰዎች የምግብና የውሃ ርዳታ እየጠበቁ
በሶማሌ ክልል በዋርዴር ወረዳ በድርቁ የተጎዱ ሰዎች የምግብና የውሃ ርዳታ እየጠበቁ

ለዚህም ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ እና ከለጋሾች የተገኘው ምላሽ አጥጋቢ ባለመኾኑ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት በጋራ ሆነው በድርቁ ለተጎዱ ሰዎች የዕለት ደራሽ የምግብ ርዳታ እያቀረቡ መሆኑን የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ከመንግሥቱ ጋር በጋራ የሚሠሩ የሰብዓዊ ረድኤት ድርጅቶች በተለያየ ጊዜ ለአሜሪካ ደምጽ ተናግረዋል።

አቶ ጉዩ ሃለኬ በቦረና ዞን ዱብሉቅ አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደር ናቸው። የዚህ ዓመት ድርቅ አካባቢያቸውን ማድረቅ ከጀመረ ከጥር ወር ጀምሮ ከብቶቻቸው እንዳለቁባቸው ነግረውን ነበር።አቶ ጉዩ በጥር ወር ስናነጋግራቸው ከ30 ከብት ዐሥር እንደሞተባቸውና ሃያ እንደቀራቸው ገልፀው ሁሉም ያልቁብኛል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረው ነበር።

ከአራት ወራት በኋላ ስንጠይቃቸው “ሃያ ስምንት ሞተው ሁለት ቀርተውኛል። ይኸው ዛሬ አንዱ ሞቶብኝ አውጥቼ ጣልኩት።” ብለዋል።አቶ ጉዩን እርሳቸና ቤተሰቦቻቸው የሚመገቡት ስንዴና በቆሎ በእርዳታ ቢያገኙም ከብቶቻቸውን ግን ከሞት የሚታደጉበት ምንም ነገር እናዳላገኙ ይናገራሉ።

ባልደረባችን እስክንድር ፍሬው ወደ ሶማሌ ክልል ኮርኔ ዞን ኩትንብ ወረዳ ተጉዞ ያገኛቸው አቶ አብዱላሂ ካሊፍ ከነበሯቸው 100 ፍየሎችና 250 ግመሎች የበዛውን በድርቅ አጥተው 50 ብቻ እንደቀራቸው ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በድርቁ የተከሰተው የእንስሳት ሞት ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀው የቀሩትን ለማትረፍ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ።በደቡብ ክልል ድርቁ በተከሰተበት አካባቢ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ነዋሪ እየተሰጣቸው ያለው እርዳታ በቂ እንዳልሆነ ገልፀው የእንስሳት ሞት በብዛት እንዳለ ይናገራሉ።

“ገጠር አካባቢ ያሉ ሰዎች ድንች ከመሬት ውስጥ እየቆፈሩ ይበላሉ። እንስሳት ግን እንዳለ እያለቀ ነው፡” ይላሉ።ድርቁ ከተከሰተባው አንዱ አማራ ክልል ዋግምራ አካባቢ ነው። በዚህ አካባቢ ውርጭ፣ በረዶና ጎርፍ በመከሰቱ አሁን የጨመረው የተጎጂዎች ቁጥር ይህን አካባቢም እንደሚያካልል ተነግሯል። በዚህ አካባቢ ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ ከሁለት ወር በፊት ስለ መኖሪያ ቀያቸው ጠይቀናቸው “እኛ አካባቢ ትልቁ ችግር የመሬት ጥበት ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውን ነበር።

በባሌ ዞን በዳሎመና ነዋሪ የሆኑና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ በባሌ ዞን ብሔራዊ ፓርክና በአቅራቢያው ያሉ ዞንና ወረዳዎች በድርቅ መጎዳታቸውን ደንና የውሃ ኩሬዎች በአሳዛኝ ሁኔታ መድረቃቸውን ተናግረዋል። የሥራ አጥ ቁጥር መጨመሩንም ገልፀዋል። እንዲህም ሆኖ ከፌደራል መንግሥትና ከለጋሾች የሚመጣው ርዳታ በአግባቡ እንደማይሰጣቸው ይናገራሉ።

ድርቁ ይፋ ከተደረገበት ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ የግጦሽ መሬትና የውሃ ኩሬዎችን ጭርሱኑ ማድረቁን፣ የአርብቶ አደሮች የኑሮ መሰረት የሆኑትን እንስሳት መጨረሱ ሲዘገብ ቆይቷል። ሥራ ማጣት፣ መፈናቀል እና ተማሪዎች ከትምሕርት ገበታቸው መፈናቀል ተዘግቧል።

በአንፃሩ ኮሚሽኑ የተፈናቀሉት ሰዎች ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ የተዘዋወሩ ናቸው ይህ ደግሞ ተረጂዎቹን በአንድ ቦታ አግኝቶ ለመርዳት ያግዛል ብሏል። ተማሪዎቹም በምገባ ፕሮግራም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንደተመለሱ ይገልፃል።

ከእነዚህ መግለጫዎች በኋላ ኮሚሽኑ እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ለቪ.ኦ.ኤ እንዳስታወቁት የተጎጂዎች ቁጥር በመጨመሩ የሰብዓዊ እርዳታ መጠየቂያው ሰነድ (HRD) ተከልሷል።

የተረጂዎች ቁጥር በ2.2 ሚሊዮን ጨምሮ 7.8 ሚሊዮን ሆኗል። ይህ የኾነው ደግሞ አስቀድሞ ለ5.6 ሚሊዮን ሕዝብ የተፈለገው 1 ቢሊዮን ዶላር ሳይገኝ ነው።

የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንደተናገሩት፤ “እስካሁን ከዚህ ገንዘብ የተገኘው የአሜሪካ መንግስት በዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (WFP) እና በጃይንት ኢመርጀንሲ ኦፕሬሽን አማካኝነት የሰጡት 114 ሚሊዮን ዶላር ነው።” ብለዋል።

የኮሚሽኑ ኃላፊ መንግሥት ድርቁን ለመቋቋም እየሠራ መሆኑን ርዳታውንም በአግባቡ ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ። “ረሃብ” የለም ሲሉም ይከራከራሉ፡ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የነገሌ ቦረና ነዋሪ “ሌሎች እንዴት እንደሚታያቸው አላውቅም እንጂ እኛ አካባቢ ድርቁም ከፍተኛ ነው ረሀብም አለ” ይላሉ”

ለጋሽ ድርጅቶች በቀጣይ ተመጣጥኝ ዝናብ ካልዘነበና የተጠቀሰው ገንዘብ መገኘት ካልቻለ አደጋው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ሥጋታቸውን ከወዲሁ እየገለጹ ነው።የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ እስካሁን አጥጋቢ እርዳታ ባይገኝም የፌደራል እና የክልል መንግሥታት በጀት መድበው እርዳታ እያደረጉ ነው ብሏል።

ስለ ሰብዓዊ ጉዳዮች የዜና ትንታኔ እና ዘገባ በማቅርብ የሚታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዜና ወኪል (ኢሪን) በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት የመሳሰሉ አባባሽ ምክንያት ባይኖሩትም “አደጋው ግን ቀላል አይደለም” ብሏል።

በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥረት ተጋልጦ እንደነበር ይታወሳል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG