በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ ከተሞች ዛሬም ሰልፎች ነበሩ፤ የመንግሥት አካላት መልስ ሰጥተዋል


የኦሮሚያ ክልል ካርታ /ምንጭ - ተመድ/
የኦሮሚያ ክልል ካርታ /ምንጭ - ተመድ/

በኦሮሚያ - ጊንጪ ከተማ ህዳር ዘጠኝ ቀን የጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ ዛሬም በምዕራብ ወለጋ ሁለት ከተሞች መቀጠሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቪኦኤ ገልፀዋል።

please wait

No media source currently available

0:00 0:08:46 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

በኦሮሚያ - ጊንጪ ከተማ ህዳር ዘጠኝ ቀን የጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ ዛሬም በምዕራብ ወለጋ ሁለት ከተሞች መቀጠሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቪኦኤ ገልፀዋል።

በምዕራብ ወለጋ በመንዲ እና ጉሊሶ “መንግሥት አድማ በታኞችንና የአግዓዚ ጦርን አሠማርቶ ብዙ ተማሪዎችንና የከተማዪቱን ነዋሪዎች በቁጥጥር ሥር አውሏል” ሲል አንድ ስሙ እንዳይገለፅ የጠየቀ ነዋሪ ከቪኦኤ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ገልጿል።

“በተጨማሪም ከላይ በተጠቀሰው ዞን ውስጥ ጉሊሶ በተባለ ከተማም እንዲሁ ዛሬው ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ እንደተሰባሰቡ ፖሊስ በአድማ በታኝ ጢስ ሠልፉን በትኗል” ስትል አንዲት ተማሪ ገልፃለች።

በጉሊሶ ወረዳ የሰላም እና መረጋጋት ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍቅሩ ሙለታ “ተማሪዎቹ ሠላማዊ ሰልፍ የማካሄድ ፈቃድ ሳይሰጣቸው የወጡ በመሆኑ እንዲበተን አድርገናል” ብለዋል፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ጊንጪ ከተማ ባለፈው ሣምንት የተካሄደውን የተማሪዎች ተቃውሞ ተከትሎ “ሰባ ሰዎች ታስረዋል፤ ብዙዎች ተደብድበዋል” ሲሉ የከተማዪቱ ነዋሪዎችና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ፀሐፊ አቶ በቀለ ነጋ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

“ጊንጪ ከተማ የሚገኘው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሬት ተቆርሶ ለግለሰብ ተሸጧል። የጊንጪ ከተማ ስታዲየም ላልታወቀ አካል ተሸጧል። የጪሊሞ ደንም እንዲሁ ለግለሰብ ተሸጦ የዛፍ ቆረጣ ተጀምሯል። ይህን ሁሉ እንቃወማለን” ብሏል አንድ የከተማው ነዋሪ።

ነዋሪው አክሎም “የመንግሥት አካላት ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት ይልቅ ልጆቹን በዱላ ተቀብለዋቸዋል። ዕለቱ የገበያ ቀን ስለነበረ የከተማው ነዋሪ እና ገበያተኛም ተማሪዎች በአድማ በታኝ ፖሊስ ሲደበደቡ ሲያዩ በመቃወማቸው እነርሱም ተደብድበዋል። አድማ በታኞቹ ሁሉም ዱላ ይዘዋል። ዱላውንም ተጠቅመውበታል” ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹ በወቅቱ በመንገድ ላይ ሲያልፍ የነበረው ሰላም ባስ ላይ ድንጋይ በመወርወራቸው ድብደባው ተባብሶ እንደነበርም ገልጸዋል። ።

ተቃውሞውን አስመልክቶ የተናገሩት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ጸሐፊ አቶ በቀለ ነጋ “የተቃውሞው መንስዔ የመንግሥት አካላት የትምህርት ቤት መሬት ቦታ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው ሲሆን ለተማሪዎች በሃገሪቱ ሕግ መሠረት መልስ ከመስጠት ይልቅ የመንግሥት አካላት ተማሪዎችን በመደብደብና በማሰር ላይ ናቸው” ብለዋል። በነጆ ከተማ ብቻ የአሥራ አራት ቤተሰቦች ቤት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መፈተሹን ገልፀዋል።

“የሚደረጉት ነገሮች የሀገሪቱን ሕግ የሚሰብሩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ከምርጫ በፊት የታሰሩ ሦስት አባሎቻችንን በዱላ ደብድበዋል፤ መዝገቡ ደበላ እና መምህር ዘላለም ሚስማ ‘ምንም ጥፋት አልተገኘባቸውም’ ተብሎ ከአንድ ዓመት ከሦስት ወር በኋላ ተለቅቀዋል። ለዚህ የሚጠየቅ አካልም የለም” ብለዋል አቶ በቀለ ነጋ።

አቶ በቀለ እንደሚሉት በአምቦው ሠልፍ ላይ ተማሪዎች “የኦሮሞ መብት ይከበር፤ ማስተር ፕላኑን ጨምሮ የመሬት ዝርፊያ ይቁም” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። ሠልፉም በሰላም ተጠናቅቋል።

በመንዲ ከተማም እንዲሁ የተማሪዎች ሰልፍ የተካሄደ ሲሆን እዚያም የገበያ ቀን ስለነበር ህዝቡም አብሮ ሲቃወም ውሏል ሲሉ አንድ የከተማዪቱ ነዋሪ ገልፀውልናል።

“ቡራዩ የኦሮሞ ነው፤ ሰበታ የኦሮሞ ነው፤ ገላን የኦሮሞ ነው” “ የሚሉ መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን የቪኦኤው ነሞ ደንዲ ነዋሪዎቹን እያነጋገረ በነበረበት ወቅት ሲያነጋግር በነበረበት ወቅት ተኩስ ይሰማ ስለነበር ሁኔታውን ሲጠይቀው ነዋሪው “ተኩሱ እንደዝናብ እየወረደ ነው፤ የሚተኩሱት ግን ወደ ሰማይ ነው፤ ፈጥኖዎች ተማሪዎችና ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ እያደረሱ ነው፡፡ አቶ ሄኖክ ዳግም የተባለ ነጋዴ ቤቱ ፊት ለፊት እንደቆመ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶበታል” ብሏል፡፡

በተለያዩ ከተሞች ተካሄዱ የተባሉትን የተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፎች አስመልክቶ በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሺን የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰሎሞን ታደሰ በሀገሪቱ የተረጋጋ ሕይወትና ሰላም መኖሩን ገልፀው ማንም ‘አለ’ የሚለውን ችግር ከሚመለከተው አካል ጋር በውይይት መፍታት እንጂ ጥቂት ተማሪዎች በሚያነሱት ብጥብጥ የህዝቡን ሰላም ማደፍረስ የለበትም” ብለዋል።

ባለሥልጣኑ አቶ ሰሎሞን “ሰባ ሰዎች ታስረዋል የሚባለው ውሸት ነው። አሥራ አራት ተማሪዎች በኅብረተሰቡ ሰላም ላይ ችግር ሲያደርሱ ሕግ በሚፈቅደው መንገድ ቁጥጥር ሥር ውለዋል። ይህ ፍርድ ቤት የያዘው ጉዳይ ነው ። የተደበደበ ተማሪ የለም” ብለዋል።

“በመንዲ፣ ቂልጡ፣ ካራ፣ አምቦ፣ ነጆና ሌሎች ከተሞች ውስጥ ተቃውሞ ቀጥሏል፤ ድብደባም ይፈፀማል ይባላል፤ ሰዎች ሳነጋግር እኔው ራሴም ተኩስ ሰምቻለሁ” ብሎ ነሞ ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሰሎሞን መልስ ሲሰጡ “የደረሰን ሪፖርት የለም። ነገር ግን ችግር ካለ፣ በመንግሥት በኩል ስህተት ካለ በሰላማዊ መንገድ መጠየቅና መፍትኄ መፈለግ እንጂ ረብሻ መፍትኄ አይሆንም፤ በጀልዱ ማስተር ፕላኑን አስመልክቶ ተማሪዎች ጥያቄ አንስተዋል ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ ተስማምተው ሠልፉ በሰላም ተጠናቅቋል፤ ማስተር ፕላኑን በደንብ ያለመረዳት ችግሮች ይታያሉ” ሲሉም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሺኑ የከምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሰሎሞን ታደሰ አስረድተዋል።

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG