በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ትኩረት


ፎቶ ፋይል፦ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
ፎቶ ፋይል፦ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

ከነገ ጀምሮ አዲስ አበባ ላይ ለሁለት ቀናት ሚካሄደውና 55 አባላት ያሉት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ተጠይቋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምሕሩ ዶ/ር ንጉስ በላይ፤ የአፍሪካ መሪዎች አህጉሪቷ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ከተረጂነት ልትወጣ የምትችልበትን አጀንዳ ተግባራዊ ሊያደርጉት እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ግጭቶች መበራከታቸውን የገለፁት ድ/ር ንጉስ በላይ “አፍሪካውያን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፀጥታ ችግር ስላለብን የአፍሪካ መሪዎች ሰላም የምጣትን ጉዳይ ተኩረት ሰጥተው የሚወያዩበት ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል በዚህ የመሪዎች ስብሰባ በህወሓት ታጣቂዎችና በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም ኤርትራን ጨምሮ በአጋሮቻቸው መካከል በሚደረገው ጦርነት ውስጥ የደረሰውን ሰፊ ጥቃት ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲመለከተው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሂዩማንስ ራይትስ ወች ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

ድርጅቱ በመግለጫው በኅብረቱ ስብሰባ ላይ የዲምፕክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቺሴኬዲን ተክተው የሕብረቱ ሊቀመንበር ሆነው የሚመረጡት የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል፣ ሰብዓዊ መብት፣ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት የህብረቱ ቀዳሚ አጀንዳ እንዲሆን እንዲያደርጉም አሳስቧል።

የሂዩማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ድይሬክተር የሆኑት ካሪን ካኔዛ ናንቱሊያ "የአፍሪካ ህብረት አባላት የኢትዮጵያ መንግሥትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የተሳተፉት ሁሉም አካላት የፈፀሙትን ከፍተኛ ወንጀል በቸልተኝነት ሊያልፈው አይገባም።" ብለዋል።

መግለጫው አክሎ በቡርኪናፋሶ፣ በቻድ፣ በጊኒ፣ በማሊ እና በሱዳን የተካሄዱትን መፈንቅለ መንግሥቶች ጨምሮ፣ መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚደረጉ ሙከራዎችና ወታደራዊ ኃይሎች ስልጣን መቆጣጠር ባለፈው ዓመት እየጨመረ መምጣቱ ጠቅሷል።

ይህም ሕዝብ የራሱን መንግሥት መምረጥ እንዳይችል እያደረገውና ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያጋለጠ መምጣቱን በመጥቀስ የአፍሪካ ህብረት ገደብና ተጠያዊነት የሌለውን ስልጣን እንዲያግድ፣ የምርጫ መጭበርበሮችና የፖለቲካ ጭቆናዎችን የሚያስቀሩ ጠንካራ ፖሊሲዎችንም እንዲያወጣ ጠይቋል።

የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ኃላፊነታቸውን የሚረከቡት፤ እነዚህ ሁሉ የፀጥታና የጤና ችግሮች በአህጉሪቱ ላይ በበረከቱበት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ብጥብጦችና አለመረጋጋቶች በተዛመቱበት ወቅት መሆኑን ያሰመሩበት ካኔዛ ናንቱሊያ፣ ፕሬዚዳንት ሳል የአፍሪካ ህብረት በተመሰረተበት ዋና መርህ መሰረት መንግሥታት የሚያደርሷቸውን ጥቃቶች ላይ ጤንካራ አቋም በመያዝ፣ ተጠቂዎች ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግና ከቀሪው ዓለም ጋር እኩልነትና ሚዛናዊ የኾነ ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ ጠንካራ አመራር ማሳየት ይችላሉ ብለዋል።

በየጊዜው ከሚደረግ ውይይት ባለፈ መሪዎቹ ለአጀንዳው ተፈፃሚነት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በዚህ ዙሪያ የተሰናዳውን ዝርዝር ዘገባ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ትኩረት
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:38 0:00


XS
SM
MD
LG