በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዐማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲታወጅ ተወሰነ


የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ዛሬ ዐርብ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ያካሔደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ ፎቶ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ዛሬ ዐርብ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ያካሔደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ፤ ፎቶ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ዛሬ ዐርብ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በአካሔደው 23 መደበኛ ስብሰባ፣ በዐማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲታወጅ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዲሬክተር ጀነራሉ የሚመራና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የኾነ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያም ተቋቀሟል። የሥራ ጊዜው ለስድስት ወራት ነው።

ምክር ቤቱ በክልሉ ያለውና ሕገ ወጥ ሲል የገለጸው ትጥቃዊ እንቅስቃሴ፣ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዐት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት አዳጋች ደረጃ እንደተሸጋገረ አመልክቷል፡፡

በመኾኑም፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ኾኖ እንደተገኘ የገለጸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቁጥር 6/2015 እንዲታወጅ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

“እንቅስቃሴው፥ በሀገር ደኅንነት እና በሕዝብ ሰላም ላይ የደቀነው አደጋ፣ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል፤” ሲልም ገልጿል፡፡የዐማራ ክልል መንግሥትም፣ የፌዴራል መንግሥት፣ “በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት፣ አስፈላጊውን የሕግ ማኅቀፍ እንዲደነግግና ተገቢውን ርምጃ እንዲወስድ” ትላንት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ትጥቅ አንሥተው የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ኹሉ፣ ሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድን እንዲከተሉ፣ መንግሥት፣ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ሲያደርግ እንደቆየ አውስቶ፣ ነገር ግን “የታጠቁ ጽንፈኛ ቡድኖች” ያላቸው አካላት እየፈጸሙ ባለው ጥቃት ምክንያት፣ “በክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፤” ሲል አመልክቷል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በሕገ መንግሥቱ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱ ላይ የተቃጣን አደጋ፣ በመደበኛ የሕግ ሥርዓት ለመቆጣጠር ባልተቻለ ጊዜ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የማወጅ ሥልጣን አለው፡፡ ይኹንና፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ባለመኾኑ፣ ዐዋጁ በ15 ቀናት ውስጥ ለምክር ቤቱ ቀርቦ መጽደቅ እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወቅትም፣ ሰብአዊ መብቶች ሊከበሩ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ፣ በሕገ መንግሥቱ እና ኢትዮጵያ ተቀብላ በአጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዕውቅና ያገኙ ሰብአዊ መብቶችንና የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መርሖዎችን በአከበረ መልኩ እንዲተገበር፣ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

ኮሚሽኑ አክሎም፣ “ኹሉም ወገኖች፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፣ ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጡና ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶችም እንዲቆጠቡ…፤” ሲል ጠይቋል፡፡

መንግሥት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችንና ኢ-መደበኛ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ መደበኛ የጸጥታ ተቋማት የማካተት ፕሮግራም ከዘረጋ በኋላ፣ በዐማራ ክልል ውሳኔውን የመተግበር እንቅስቃሴ ከጀመረበት፣ ካለፈው ሚያዝያ ወር አንሥቶ፣ በክልሉ የትጥቅ ግጭቶች ሲስተዋሉ ቆይተዋል፡፡ እነዚኽም ግጭቶች፣ በአሁኑ ወቅት እየተስፋፉ እና እየተባባሱ ሔደዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም፣ በልዩ ልዩ የክልሉ አካባቢዎች፣ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል የተኩስ ልውውጦች እየተካሔዱ እንደሚገኙ፣ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG