በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሁለት ኢትዮጵያዊያን በሊቢያ መሞታቸውንና በርካታዎች መሰወራቸውን ስደተኞቹ አስታወቁ


አንደ ቤንጋዚ ባሉ ከመንግስት ቁጥጥው ውጭ በሆኑ ስፍራዎች በአፍሪካዊያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት የከፋ ነው
አንደ ቤንጋዚ ባሉ ከመንግስት ቁጥጥው ውጭ በሆኑ ስፍራዎች በአፍሪካዊያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት የከፋ ነው

የጋዳፊ ቅጥረኞች ናችሁ በሚል ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ጥቃት እየደረሰባቸው ነው

በጸረ-መንግስት ተቃውሞዎች የተናወጠችውን ሊቢያ ለቀው ለመውጣት በርካታ ሽህ የውጭ አገር ስደተኞች በአውሮፕላን፤ በመርከብና በእግር እየተመሙ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን በከባድ ችግር ውስጥ ወድቀዋል።

በዚህ ግጭት መሀል የተያዙት በሊቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ስደተኞች የሞማር ጋዳፊ ቅጥረኛ “ጥቁር የውጭ አገር ወታደሮችሁ” ናቸው በሚል ለድብደባ፣ ዘረፋና ግድያ መጋለጣቸውን ይናገራሉ።

በጸረ-መንግስት ተቃውሞ በታወከችው ሊቢያ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ከቤታቸው አይወጡም። ወጥቶ ለቤተሰብ፣ በተለይ ለልጆች የሚቀመስ እህል ውሃ መግዛት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

እነዚህ ስደተኞች በአንድ በኩል በሁከት በሌላ በኩል የጋዳፊ ቅጥረኛ የውጭ አገር ተዋጊዎች ላይ ባለው ጥላቻ ከባድ ችግር ላይ ወድቀዋል።

“ጥቁር መንገድ ላይ ከወጣ መግደል ነው” ይላል በሊቢያ ለ9አመት የኖረው ኢትዮጵያዊ ሳሚ።

ወደ ሱቅ ሄዶ ምግብና ውሃ መግዛት በህይወት ዋጋ የሚያስከፍልበት ደረጃ ደርሰናል ይላል።

“ለቤተሰባቸው ምግብ ሊገዙ የወጡ ሶስት ኢትዮጵያዊያን አንዱ የአሩሲ ልጅ ነው። እግሩን በጥይት መትተው ይዘውት ሄደዋል” ይላል ሳሚ።

በመንግስት ቁጥጥር ስር በማይገኙ ከተሞች። ማለት የጸረ-ጋዳፊ ተቃዋሚዎች ነጻ ባወጧቸው ከተሞች በጥቁር አፍሪካዊያን ላይ ያለው ቁጣ በጣም ያየለ ነው። ሳሚ ሁኔታው ከቆየ ጥላቻ የመነጨ ቢሆንም፤ በአልጀዚራ ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ ፓስፖርት ያላቸው ሰዎች በጋዳፊ ቅጥረኛ ተዋጊነት ተጠርጥረው ከተያዙ ወዲህ ቁጣው ወደ ጥቃት ተለውጧል።

በጠቅላላው ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ እነዚህ ስደተኞች ከባድ የሆነ ችግርና ጥቃት ይደርስባቸዋል በሚል ተሰግቷል። የሊቢያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች መስሪያቤትን ከሀገር እንዲወጣና ስራውን እንዲያቆም ማድረጉ ይታወሳል።

በዚህ እርምጃ ወደ 12ሽህ የሚሆኑ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎችና ሌሎች ስደተኞች አስተባባሪ አጥተው ቆይተዋል። ከነዚህ መከከል በሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ይገኙበታል።

UNHCR እና ሌሎች አለማቀፍ የስደተኛ ተቆርቛሪ ድርጅቶች በሌሉበት ሁኔታ፤ አገሮች ዜጎቻቸውን በአውሮፕላን በመርከብና በመኪና እያስወጡ ባለበት ወቅት፤ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያን፣ ሱዳናዊያን እና ሌሎችም በከባድ ችግር ላይ ናቸው።

አንድ በጣሊያን መሰረቱን ያደረገ አጄንሲያ አበሻ የተባለ ማህበር፤ የአውሮፓ ህብረት በተለይ ደግሞ የጣሊያን መንግስት ዜጎቻቸውን ከሊቢያ ሲያወጡ፤ ኢትዮጵያዊያኑንና ኤርትራዊያኑን አብሮ ከሀገር እንዲያወጣ በመማጸን ላይ ነው።

“ከአውሮፓዊያን ዜጎች ጋር አብሮ የመውጣት እድል እንዲሰጣቸው ጠይቀናል” የሚሉት አባ ሙሴ ዘርዓይ አጀንሲያ አበሻ የተባለው ማህበር መስራች ናቸው። የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በትሪፖሊ ለሚገኘው ኢምባሲ ሁኔታውን እንዲያሳውቅና የስደተኞቹ ደህንነት እንዲጠበቅ ያቀረቡት ጥያቄ፤ በጣሊያን መንግስት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አላገኘም። የስደተኞቹ ቁጥር በርካታ በመሆኑ ከሊቢያ ማውጣቱ ከባድ እንደሆነ መልስ ተሰጥቷቸዋል። አባ ሙሴ ትግላቸውን አላቆሙም። ህጻናት ልጆች ላላቸው ቅድሚያ እንዲሰጥ የተረፉትን ደግሞ ወደ ጎረቤት አገሮች እንዲዛወሩ እየወተወቱ ነው።

አባ ሙሴ በዚህ ትግላቸው ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

XS
SM
MD
LG