በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የእምነት ተቋማትን በራሱ ላለማፍረስ ተስማማ 


የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የእምነት ተቋማትን በራሱ ላለማፍረስ ተስማማ 
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:08 0:00

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የእምነት ተቋማትን በራሱ ላለማፍረስ ተስማማ 

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ ሕዝበ ሙስሊሙ፥ በሸገር ከተማ እና በመላው የኦሮሚያ ክልል ለሚያቀርባቸው የመስጊድ ጥያቄዎች፣ በማስተር ፕላኑ መሠረት ምላሽ ለመስጠት መስማማቱ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋራ፣ ሰፊ ውይይት መደረጉን አስታውቋል፡፡

በውይይቱም፣ የክልሉ መንግሥት፣ ከእንግዲህ መፍረስ ያለባቸውን አብያተ እምነት፣ ራሳቸው የእምነት ተቋማቱ እንዲያፈርሱ እንጂ፣ በራሱ ማፍረስ እንደሚያቆም መስማማቱ ተገልጿል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ በመነጋገር እና በመወያየት ችግሩ መፍትሔ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡ ገብረ ሚካኤል ገብረ መድኅን ዝርዝር አለው፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ በሸገር ከተማ እየተካሔደ ባለው የመስጊድ ፈረሳ ጉዳይ፣ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ ጋራ አምስት ሰዓታትን የፈጀ ሰፊ ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የም/ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ በሸገር ከተማ ታይቶ በማይታወቅ ኹኔታ ብዛት ያላቸው መስጊዶች መፍረሳቸውን አመልክተው፣ አሁን ግን ችግሩ መፍትሔ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

በሸገር ከተማ፣ እስከ አሁን ድረስ 22 መስጊዶች እንደፈረሱ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት፣ የመስጊዶችን መፍረስ በማውገዝ፣ የጁመዓ ሶላት ሥነ ሥርዐት ከተጠናቀቀ በኋላ ተቃውሞዎች ሲደረጉ ሰንብተዋል፡፡ በተለይም፣ በታላቁ አንዋር መስጊድ እና አካባቢው በተካሔደው ተቃውሞ፣ የሰው ሕይወት ማለፉንና በርካቶች መጎዳታቸውን፣ በጊዜው ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ እማኞች ገልጸዋል፡፡ በሌሎች መስጊዶችም እንዲሁ፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ነበር፡፡ በሸገር ከተማ፣ ከመስጊዶች በተጨማሪ፣ በርካታ የመኖሪያ ቤቶችም መፍረሳቸው ተገልጿል፡፡

በዛሬው መግለጫ፣ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጋራ በተደረገው ውይይት፣ የተለያዩ ነጥቦች እንደተነሡ፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የአደረጃጀት እና የማኅበራዊ ዘርፍ ሓላፊ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ጠቅሰዋል፡፡

እርሳቸው ባነበቡት የምክር ቤቱ መግለጫ ላይ፣ በውይይቱ ወቅት፣ በአገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች፣ ለመስጊድ ግንባታ መሬት በሕጋዊ መንገድ ማግኘት እና ለተሠሩትም መስጊዶች ካርታ የመረከብ ችግሮች እንዳሉ ተነሥቷል፤ ብለዋል፡፡ የሸገር ከተማ አስተዳደር፣ መስጊዶችን ከማፍረሱ በፊት፣ ከእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ጋራ አለመወያየቱ፣ በቅሬታ መልክ እንደቀረበም ተናግረዋል፡፡ ከዚኹ ጋራ የተያያዙ ሌሎችም ነጥቦች እንደተነሡ፣ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ጠቁመዋል፡፡

ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ፣ መስጊዶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ውይይት አለመደረጉ፣ ስሕተት እንደኾነና በተፈጠረው ኹኔታም ሕይወት በማለፉ እንዳዘኑ ተገልጿል፡፡ አቶ ሺመልስ፣ የሸገር ከተማ፣ ሃይማኖታዊ ዕሤትን መሠረት አድርጎ እንደሚገነባና ለከተማዋ ፕላን የሚመጥኑ በርካታ ዘመናዊ መስጊዶች እንዲሠሩ ፍላጎታቸው እንደኾነ ጠቅሰዋል፤ ተብሏል፡፡ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ በሌሎች መሰል ጉዳዮችም ቃል እንደገቡ፣ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል አመልክተዋል፡፡

ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል በመግለጫቸው፣ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ እስከ ትላንት ድረስ፣ የታሰሩ ሙስሊሞች፣ ያለምንም ልዩነት እንዲፈቱ እንጠብቃለን፤ ካሉ በኋላ፣ በጉዳዩ ዙሪያ፣ ከዛሬ ጀምሮ ከፌዴራል እና ከዐዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮች ጋራ ውይይት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤቱ፣ የስምምነቱን አፈጻጸም እንደሚከታተል የተናገሩት፣ የም/ቤቱ ፕሬዚዳንት የሕግ አማካሪ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በበኩላቸው፣ ሕዝበ ሙስሊሙ የስምምነቱን ውጤት በትዕግሥት እንዲጠባበቅ አሳስበዋል፡፡

በሸገር ከተማ ከሚካሔደው የቤቶች ፈረሳ ጋራ ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት መግለጫዎችን አውጥተዋል፡፡ የከተማዋ አስተዳደር፣ በቤቶች ፈረሳው፥ የተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች እንዲያከብርም ጠይቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG