በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሸገር ከተማ ቤቶች ፈረሳ 100 ሺሕ አቤቱታዎች ቀረቡበት


 የሸገር ከተማ ቤቶች ፈረሳ 100 ሺሕ አቤቱታዎች ቀረቡበት
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:54 0:00

የሸገር ከተማ ቤቶች ፈረሳ 100 ሺሕ አቤቱታዎች ቀረቡበት

· “ማካካሻ አለመሰጠቱ ወይም ጊዜያዊ መጠለያ አለመዘጋጀቱ አሳስቦናል”- እንባ ጠባቂ ተቋም

በሸገር ከተማ “ሕገ ወጥ ግንባታ” በሚል እየተካሔደ ካለው የቤቶች ፈረሳ ጋራ የተያያዙ፣ 100ሺሕ አቤቱታዎች እንደቀረቡለት፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡

የተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ ዶር. እንዳለ ኃይሌ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ተቋሙ፣ በ2014 ዓ.ም. የበጀት ዓመት፣ ከመብት ጥሰት እና ከመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ጋራ የተገናኙ፣ ከ133 ሺሕ በላይ አቤቱታዎችን እንደተቀበለ አውስተው፣ ከዚኽ ውስጥ ከፍተኛውን አኀዝ የያዙት፣ በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ ካለው የቤት ፈረሳ ጋራ የተያያዙ አቤቱታዎች ናቸው፤ ብለዋል፡፡

የሸገር ከተማ አስተዳደር፣ “ሕገ ወጥ ግንባታ” እያለ ለሚያፈርሳቸው የመኖሪያ ቤቶች፣ ለነዋሪዎች ምትክ ቦታ እንደማይሰጥና ለተፈናቃዮችም ጊዜያዊ መጠለያ እንደማያዘጋጅ፣ ዶር. እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ፣ የአሜሪካ ድምፅ፣ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ሓላፊዎች አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት፣ ለዛሬ አልተሳካም፡፡

ከዚኽ ቀደም፣ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡን፣ የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶር. ተሾመ አዱኛ ግን፣ “እያፈረስን ያለነው፣ የግንባታ ፈቃድ የሌላቸውን ቤቶች ነው፤” ብለው ነበር፡፡ ርምጃው፣ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር ጋራ የተያያዘ እንደኾነ ያመለከቱት ከንቲባው ዶር. ተሾመ፣ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው አስቀድሞ፣ ከነዋሪዎቹ ጋራ ውይይት ይደረጋል፤ ብለዋል፡፡

“ሕገ ወጥ ግንባታ” በሚል ምክንያት የመኖርያ ቤቶችን ማፍረስ፣ በሁሉም ታላላቅ ከተሞች የሚስተዋል ችግር መኾኑን የጠቀሱት ዋና እንባ ጠባቂው በበኩላቸው፣ መንግሥት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፥ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ በሕዝብ ላይ ለሚፈጽሟቸው አስተዳደራዊ በደሎች የመፍትሔ ሐሳብ በማቅረብ፣ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ይሠራል፤ የሚሉት፣ የተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ ዶር. እንዳለ ኃይሌ፣ ተቋሙ ባለፈው ዓመት፣ ከአስተዳደራዊ ጉድለቶች እና ከመብቶች ጥሰት ጋራ

የተያያዙ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ አቤቱታዎችን መቀበሉን አስታውሰዋል፡፡ ከአቤቱታዎቹ የሚበዙትም፣ ከሸገር ከተማ የመጡ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

በዚኽ ጉዳይ ላይ፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋራ ቢወያይም፣ በተጨበጭ መሬት ላይ እየኾነ ያለው ነገር፣ በውይይቱ ከተነሣው የተለየ እንደኾነ፣ ዋና እንባ ጠባቂው ተናግረዋል፡፡

የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶር. ተሾመ አዱኛ፣ ቀደም ሲል ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ እያፈረስን ያለነው ሕገ ወጥ ግንባታዎችን ነው፤ ብለው ነበር፡፡ ከፈረሳው አስቀድሞ፣ ከነዋሪዎች ጋራ ውይይት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

“ሕገ ወጥ ግንባታ” ተብለው የመኖሪያ ቤቶቻቸው ለሚፈርስባቸው ዜጎች የሚሰጥ ማካካሻ አለመኖርም አሳስቦናል፤ ብለዋል ዶር. እንዳለ ኃይሌ፡፡

በሌሎች ታላላቅ ከተሞችም፣ “ሕገ ወጥ ግንባታ” በሚል ቤቶችን ማፍረስ የተለመደ ተግባር መኾኑን የጠቀሱት ዶር. እንዳለ፣ የችግሩ መንሥኤ፣ ከከተሞች መስፋፋት ጋራ ተያይዞ የመጣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ማደግ ስለኾነ፣ መንግሥት ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ፣ በአገሪቱ ውስጥ፣ ወደ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰብአዊ ርዳታ የሚሹ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የተናገሩት ዶር. እንዳለ፣ በዚኽ ላይ ተጨማሪ ሰዎችን ማፈናቀል አግባብ እንዳልኾነ አስገንዝበዋል፡፡

XS
SM
MD
LG