በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኬንያ፤ የአዲስ መሪ ምርጫ ከአሮጌ ፊቶች


መራጮች ድምፅ እየሰጡ
መራጮች ድምፅ እየሰጡ

በፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩ እየመሩ ያሉት ራይላ ኦዲንጋና ዊሊያም ሩቶ ባሉባቸው የኬንያ አካባቢዎች ዛሬ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በረጃጅም ሰልፎች ተሞልተው ውለዋል። በሌሎች የምርጫ አካባቢዎች የተገኙት መራጮች ደግሞ ብዙ ቅሬታ ያሉባቸው፤ ሆድ የባሳቸው ናቸው - ሮይተርስ እንደዘገበው።

ኬንያ ፕሬዚዳንታዊ፣ የፓርላማ እና የአካባቢ ምርጫዎችን የምታካሂደው ባሻቀበው የምግብ ዋጋና ሥር በሰደደው ሙስና ዜጎቿ ከፍተኛ ቅሬታ ውስጥ ባሉበት ጊዜ ነው።

“ሁለቱም ተፎካካሪዎች ችግራቸንን አይቀርፉም” በሚል ተስፋ መቁረጥ፣ ደግሞም በድኃውና በሃብታሙ መካከል ያለው ልዩነት በመስፋቱ ብዙ ወጣት ለምርጫ አለመመዝገቡን ሮይተርስ ዘግቧል።

ዋና ከተማዪቱ ናይሮቢ ውስጥ፣ እንዲሁም ጋሪሳ እና ናይቫሻ በሚባሉ አካባቢዎች ባሉ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ላይ ዛሬ ይታዩት ሰልፎች በቀደሙት ምርጫዎች ከነበሩት ያጠሩ እንደነበሩ የዜና አገልግሎቱ አመልክቷል።

“ኬንያዊያን ጠዋት ተነስተው ምንም ለማይፈይድላቸው መንግሥት ድምፅ መስጠት ሰልችቷቸዋል። ቢሆንም ነገሮች ይቀየራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብሏል ከናይሮቢ 90 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ናይቫሻ ምርጫ ጣቢያ የተገኘው ጃሽዋ ንያንጁዊ። ጃሽዋ ባለፈው ምርጫ ለአራት ሰዓታት ተስልፎ እንደነበረ ዛሬ ግን የፈጀበት 30 ደቂቃ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል። በናይቫሻ ምርጫ ጣቢያ የተገኙ ሌሎች መራጮች ደግሞ በዋጋ ማሻቀብና በረሃብ የተማረሩ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በመጨረሻ የተከናወኑ አራት የህዝብ አስተያየት ዳሰሳ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ኦዲንጋ ከ6 እስከ 8 ነጥብ ባለ ርቀት ምርጫውን ሲመሩ ነበር። ሩቶ ይህን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን ውጤቱን “ሃሰት” ሲሉ ያጣጥላሉ።

በምዕራብ በምትገኘውና የኦዲንጋ ደጋፊዎች ምድር በሆነችው ኪሱሙ ከተማ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ሲዘፍኑና ሲደንሱ ያደሩ ደጋፊዎችን ፖሊስ በትኗል።

ተስፋ በማድረግም ይሁን በቀቢፀ ተስፋ ኬንያዊያን ዛሬ ከአሮጌ ፊቶች አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ አደባባይ ውለዋል።

[የዛሬውን የኬንያ ምርጫ እየተከታተልን ማቅረብ እንቀጥላለን]

XS
SM
MD
LG