በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሦስት ሚኒስትሮችን ሾሙ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሦስት ሚኒስትሮችን ሾሙ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:46 0:00

ተመስገን ምክትል ጠ/ሚ/ር ታዬ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሆነው ተሾሙ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀረበለትን የሦስት ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ ባለሥልጣናትን ሹመት አጽድቋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዲሬክተሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ የነበሩት ጎምቱ ዲፕሎማቱ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

ዛሬ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ። /ፎቶ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፌስ ቡክ ገፅ/
ዛሬ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ። /ፎቶ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፌስ ቡክ ገፅ/

ሁለቱ ተሿሚዎች ከዚህ ቀደም በአቶ ደመቀ መኰንን በአንድ ላይ በተያዙ የሹመት ቦታዎች የተመደቡ ናቸው። ከዛሬው ተሿሚዎች ተርታ የሆኑት የማሕፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር መቅደስ ዳባ ደግሞ፣ ዶ/ር ሊያ ታደሰን ተክተው የጤና ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ዶ/ር መቅደስ ጄኔቫ በሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት የምክትል ዳይሬክተሩ ልዩ ረዳት እና ከፍተኛ ባለሞያም ሆነው በማገልገል ላይ እንደነበሩ ተገልጿል።

ዛሬ ጥር 30/2016 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴና ጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ። /ፎቶ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፌስ ቡክ ገፅ/
ዛሬ ጥር 30/2016 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴና ጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ። /ፎቶ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፌስ ቡክ ገፅ/

በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በዛሬው ዕለት በዋና ዲሬክተር ማዕርግ ሁለት ከፍተኛ ሹመቶችን እንደሰጡ የመንግሥት ብዙኀን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡ በዚህም መሠረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ ዛሬ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ተመስገን ጥሩነህን በመተካት የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዲሬክተር፤ ትዕግሥት ሐሚድ ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዲሬክተር ሆነው እንደተሾሙ ተመልክቷል፡፡

በቅርቡ በገዢው ፓርቲ ከነበራቸው የምክትል ፕሬዚዳንት ኃላፊነት በክብር የተሸኙት አቶ ደመቀ መኰንን፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ ለ11 ዓመታት ከሠሩበት የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚነት ኃላፊነታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰናብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሦስቱንም ሹማምንት የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድ እና ቤተሰባዊ ሁኔታ በዝርዝር ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ሹመቱን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል። ሦስቱም ተሿሚዎች በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡

ከሦስቱ የዛሬ ተሿሚዎች ሁለቱ ማለትም አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ አባላት ውጭ እንደሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲያቸው ሦስት ወራትን የፈጀ ውይይት ካደረገ በኋላ ዕጩዎቹ ያላቸውን ልምድ እና ዕውቀት ብቻ መስፈርት አድርጎ በመምረጥ እንዳቀረባቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡

ባላቸው የሥራ ልምድ ኢትዮጵያን ለማገልገል የሚችሉትን ወደ ከፍተኛው የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚነት የማምጣቱ አሠራር፣ ለወደፊቱም ከየትኛውም ፓርቲ ቢሆን እንደሚቀጥል ዐቢይ አሕመድ ጠቁመዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG