በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውጥረትን እንዲያረግቡ ተጠየቁ


የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ እና በተገንጣይዋ ሶማሊላንድ መካከል፣ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ እየተካረረ ባለው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አለመግባባት ላይ፣ ዛሬ ረቡዕ የተነጋገረው የአፍሪካ ኅብረት የጸጥታው ምክር ቤት፣ ሁለቱ መንግሥታት ስሜትን ከተሞሉ መግለጫዎች ተቆጥበው ውጥረትን እንዲያረግቡ ጠይቋል።

በተጨማሪም፣ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ውይይትን የሚያስጀምርና ተከታታይ ሪፖርት የሚያቀርብ ልዑክ እንዲመደብ የጠየቀው የጸጥታ ምክር ቤቱ፣ የኅብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ የኾኑትን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆን ጠቁሟል፡፡

ምክር ቤቱ በስብሰባው ፍጻሜ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ እና “የሶማሊያ ሰሜናዊ ክልል” ሲል በገለጻት ሶማሊላንድ መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት በከፍተኛ ኹኔታ እንዳሳሰበው ገልጾ፣ በአካባቢው ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጥር እንደሚችል ስጋቱን አመልክቷል።

ኢትዮጵያንና ሶማሊያን ጨምሮ፣ ለኹሉም አባል ሀገራት የግዛት አንድነት፣ ነጻነት እና ሉዓላዊነት ያለውን ድጋፍ እና ቁርጠኝነትም በማያሻማ መልኩ እንደሚያረጋግጥ አስታውቋል።

በዚኹ የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር አብዱላሂ ዋርፋ እና የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር አየለ ሊሬ ንግግር ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን፣ የምክር ቤቱ መግለጫ ጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ባላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነትም ኾነ በዓለም አቀፍ ግንኙነቶቻቸው፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረታዊ መርሖዎች እንዲመሩም ጠይቋል።

መግለጫው አያይዞም፣ ሁለቱ ሀገራት፣ ጠንካራ እና መልካም ጉርብትናቸውን ከሚጎዱና አሉታዊ ተጽእኖ ከሚያሳድሩ ተጨማሪ ድርጊቶች እና መግለጫዎች እንዲታቀቡ ጠይቋል፡፡ በስም ሳይጠቅስ “የውጭ አካላት” ሲል የጠራቸው ቡድኖችም፣ በሁለቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ አሳስቧል።

የምሥራቅ አፍሪካ ልማት የበይነ መንግሥታት ድርጅት(ኢጋድ) በበኩሉ፣ ለነገ ኀሙስ፣ ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ኡጋንዳ-ካምፓላ ላይ ልዩ ስብሰባ ጠርቷል፡፡ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እና ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በጦርነት በምትታመሰው ሱዳን ያለው ቀውስ፣ ስብሰባው የሚነጋገርባቸው አጀንዳዎች እንደሚኾኑ ድርጅቱ አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG