በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ቀንድ ጎርፍ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አፈናቅሏል


በጋርሰን የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በጎርፍ የተሞላ ባህላዊ መኖሪያ ቤቶች፣ ኬንያ
በጋርሰን የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በጎርፍ የተሞላ ባህላዊ መኖሪያ ቤቶች፣ ኬንያ

በአፍሪካ ቀንድ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕሬዝ ዘግቧል።

ከአውዳሚ አየር ንብረት አደጋዎች ጋር እየታገለ ባለው በዚህ ቀጠና በሚገኙት በሶማሊያ፣ በኬንያ እና በኢትዮጵያም ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ በሰሜናዊ ታንዛኒያ ውስጥ በጣለው ከባድ ዝናብም በትንሹ 20 ሰዎች በጎርፍ መሞታቸውን የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እሁድ እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኤል ኒኖ የሚል ስያሜ ከተሰጠው ተፈጥሯዊ የአየር መዛባት ምክንያት የተያያዘው ከባድ ዝናብ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው፣ ቀጠናው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ ከዳረገው፣ በ40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ አስከፊ ድርቅ እያገገመ ባለበት ወቅት ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የሶማሊያ ባለስልጣናት በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የጎርፍ አደጋ ሶማሊያ ውስጥ ከ100 በላይ ሰዎችን ህይወት ሲያጠፋ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደግሞ አፈናቅሏል። የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ በሀገሪቱ በጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 136 መድረሱን ሲያመለክት ከ460 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ መፈናቀላቸውን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ድርጅት (ኦቻ) ኢትዮጵያ ውስጥም 57 ሰዎች በጎርፍ አደጋ መሞታቸውን እና 600 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን ያመለከተ ሲሆን፣ የህፃናት አድን ድርጅት በበኩሉ ጎርፉ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው በምስራቅ ኢትዮጵያ፣ ሶማሌ ክልል በተከሰተ የኮሌራ በሽታ፣ ቢያንስ የ23 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን እና በአጠቃላይ 772 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን አረጋግጧል።

"በጎርፍ ውሃ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ማህበረሰቦች፣ መንግስት እና ለጋሾች ንፁህ የመጠጥ ውሃ እና የንፅህና አገልግሎት በማቅረብ ፈጣን እርምጃ ካልወሰዱ፣ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችላል" ሲል ድርጅቱ ጨምሮ አስጠንቅቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG