በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዐማራ ክልል የልዩ ኃይል “መልሶ ማደራጀት” ተቃውሞ የሰዎች ሕይወት እያለፈ ነው


በዐማራ ክልል የልዩ ኃይል “መልሶ ማደራጀት” ተቃውሞ የሰዎች ሕይወት እያለፈ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:36 0:00

በዐማራ ክልል የልዩ ኃይል “መልሶ ማደራጀት” ተቃውሞ የሰዎች ሕይወት እያለፈ ነው

መንግሥት የኹሉንም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ጸጥታ መዋቅሮች ለማስገባት እንደወሰነ ማስታወቁን ተከትሎ፣ በዐማራ ክልል ልዩ ልዩ ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ ግጭት ማምራቱንና የሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ገለጹ።

በደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከክልሉ ልዩ ኃይል እና የፋኖ ታጣቂዎች ጋራ በአደረጉት የተኩስ ልውውጥ፣ ሰዎች መሞታቸውን በስልክ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ግጭቱ ከተባባሰበት የከተማው ክፍል አንዱ፤ ከልዩ ልዩ የኦሮሚያ ክልል የመጡ ወደ 20ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች የሚገኙበትና “የቻይና ካምፕ” እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ሲኾን፣ ኹለት ተፈናቃዮች በተኩስ ልውውጡ ሕይወታቸው ማለፉን፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አንድ ተፈናቃይ ገልጸውልናል።

እኚኹ ነዋሪ፣ ኹለቱን ሟቾች በስም ጠቅሰው፣ በጾታ እና በዕድሜ ለይተው የነገሩን ሲኾን፤ ሕይወታቸው ማለፉን ቤተሰባቸው እስኪረዳ ስማቸውን እንድናቆየው ጠይቀውናል።

በሌላ በኩል፣ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የደብረ ብርሃን ነዋሪዋ፤ የተኩስ ልውውጡ የተባባሰው ዛሬ ቢኾንም፣ በትላንትናው ዕለት ተጀምሮ ያደረ መኾኑን ይናገራሉ።

ያነጋገርናቸው ተፈናቃይ ግለሰብ እና የከተማ ነዋሪዋ፣ በተኩስ ልውውጡ ምክንያት፣ የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎች ስለመኖራቸው ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ፥ ከከተማው አስተዳደር፣ ከፖሊስ፣ ከሆስፒታል እና ከክልሉ መንግሥት አመራሮች መረጃ ለማድረግ ያደረግነው ጥረት፤ ስልካቸው ቢጠራም ስለማይመልስ ልናገኛቸው አልቻልንም።

በዐማራ ክልል በደብረ ብርሃንም ኾነ በሌሎች ከተሞች፣ ዐመፅ እና ግጭት የተቀሰቀሰው፤ በኹሉም ክልሎች የሚገኙ ልዩ ኃይሎችን “መልሶ ማደራጀት” በሚል፣ በመንግሥት ይፋ የኾነው ፕሮግራም በገጠመው ተቃውሞ ነው።

የልዩ ኃይሎችን “መልሶ የማደራጀት ፕሮግራም” ተቃውመው ሰልፍ የሚወጡ ተቃዋሚዎች፣ “ውሳኔው ወቅቱን ያላገናዘበ ነው” ሲሉ ይተቻሉ። በክልሉ ላይ፣ ከልዩ ልዩ አቅጣጫዎች ስጋት ደቅነዋል፤ ያሏቸው ኃይሎች ትጥቅ መፍታታቸው አለመረጋገጡን፤ የዐማራ ክልል ከሚዋሰናቸው ክልሎች ጋራ የይገባኛል ውዝግብ በሚነሣባቸው አካባቢዎች ነዋሪ የኾነው ሕዝብ፣ ለጸጥታው ማስተማመኛ አለማግኘቱንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዐማራ ብሔር ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው ገና ያልተመለሱ መኾናቸውን ለተቃውሟቸው በአስረጅነት ይጠቅሳሉ።

ኾኖም ከቀናት በፊት፤ የክልሉ መንግሥት በአወጣው መግለጫ፣ “ልዩ ኃይሎችን መልሶ ማደራጀት” ሲል የጠራው እንቅስቃሴ፥ የኢትዮጵያን ህልውና የሚያበረታ፣ የመከላከያ ሠራዊትን የሚያጠናክር፣ የሕዝቦችን የጋራ ሰላም የሚያረጋግጥ፣ በኹሉም ክልሎች አመራሮች ታምኖበት የተገባባት ሥራ እንደኾነ አብራርቷል።

ስለ ጉዳዩ ከቀናት በፊት መግለጫ የሰጡት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፍአለ/ዶር./፣ በአፈጻጸም ላይ ታይቷል ባሉት ክፍተት እና በፕሮፓጋንዳ የተነሣ፣ በአንዳንድ ከተሞች የሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴዎች፣ የአድማ ጥሪ እንዲሁም የሰዎችንና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የመገደብ አዝማሚያዎች እየታዩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ይኹንና ርእሰ መስተዳድሩ፣ “የአፈጻጸም ክፍተት” በማለት የገለጹት ችግር፣ በምን ምክንያት እና በማን አማካይነት እንደተፈጠረ ያሉት ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ እሑድ ዕለት፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፣ “የአንዱ ክልል ልዩ ኃይል አሁን ትጥቅ ይፍታ፤ የሌላ ክልል ግን ይቆይ፤” የሚል ውሳኔ አለመኖሩን ጠቅሰዋል።

ይህ ውሳኔ፣ ለኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እና ለሕዝቡ ሰላም ሲባል ዋጋ ተከፍሎም ቢኾን ተግባራዊ ይደረጋል፤ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ሳይገባቸው የሚቃወሙትን ለማስረዳት እና ለማሳመን ጥረት እንደሚደረግና “ኾን ብለው የአፍራሽነት ሚና በሚጫወቱት ላይ ደግሞ ተገቢው የሕግ ማስከበር ርምጃ ይወሰዳል። ለዚኽም በቂ ዝግጅት ተደርጓል፤” በማለትም አስጠንቅቀዋል።

አንዳንድ የዐማራ ክልል ከተሞች፣ በኮሚዩኒኬሽን ቢሮዎቻቸው አማካይነት በአወጧቸው የሰዓት እላፊዎች እና የእንቅስቃሴ ገደቦች፥ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስን፣ አድማ መቀስቀስን፣ ያልተፈቀደ ሰልፍ ማድረግንና መንገድ መዝጋትን የመሰሉ ክልከላዎችን አስቀምጠዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ ወቅታዊ ኹኔታው እስከሚስተካከል ድረስ፣ ከካምፕ እንዳይወጡ ክልከላ መደረጉን፣ ያነጋገርናቸው ተፈናቃይ ገልጸውልናል። የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በአሰፈረው መልዕክትም፤ በዐማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የተከሠተውን ችግር፣ በሃይማኖት አባቶች እና በአገር ሽማግሌዎች እንዲፈታ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ በዛሬው ዕለት፣ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥም፣ የተኩስ ልውውጦች እንደነበሩ፣ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪው፣ በክልሉ የተስተዋለው አለመረጋጋት፣ ልዩ ኃይሉ ትጥቅ መፍታት የለበትም፤ ከሚለው አቋም በተጨማሪ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች የታከሉበት ነው ይላሉ።

ተመሳሳይ ተቃውሞም፣ በኮምቦልቻ ከተማ መካሔዱን እንዲሁ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን አንድ ነዋሪ በስልክ ነግረውናል።በኮምቦልቻ ከተማ፥ መንገዶችን በድንጋይ የመዝጋት፣ ጎማ የማቃጠል እና የመኪና እንቅስቃሴዎችን የገደበ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መካሔዳቸውን፣ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸውልናል።

በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን፣ በቆቦ እና በሌሎችም አካባቢዎች፣ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ መቋረጡን፤ ባንኮች እና የንግድ ድርጅቶች መዘጋታቸውን ከከተሞቹ ነዋሪዎች ገለጻ ለመረዳት ችለናል፡፡

በዐማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ በተመለከተ ዘገባ ያስነበበው የፈረንሳይ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፤ አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪን ጠቅሶ፣ ባለፈው እሑድ፣ የዐማራ ሕዝብ መብት እንዲከበር የሚጠይቁና የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚቃወሙ መፈክሮች የተሰሙበት ሰልፍ መደረጉን በዘገባው አስፍሯል።

/ሙሉ የዘገባውን ክፍል በድምፅና በምስል ተቀናብሮ ከተያያዘው ፋይል ላይ ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG