በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቆቦው ግጭት ኹለት የካቶሊክ ርዳታ ሠራተኞች ተገደሉ


ፎቶ ፋይል አማራ ክልል ቆቦ ከተማ
ፎቶ ፋይል አማራ ክልል ቆቦ ከተማ

በኢትዮጵያ የአማራ ክልል ውስጥ፣ የመንግሥትን የልዩ ኃይል መዋቅራዊ ለውጥ ውሳኔ በመቃወም በተቀሰቀሰው ሁከት፣ ኹለት የካቶሊክ ርዳታ ሰጪ ሠራተኞች መገደላቸውን፣ የርዳታ ቡድኑ አስታወቀ።

ሠራተኞቹ የተገደሉት፣ ባለፈው እሑድ እንደነበረ የጠቀሰው አሶሽየትድ ፕሬስ፣ መንግሥት በአገሪቱ የሚገኙ የ11 ክልሎች ልዩ ኃይሎችን መዋቅር አፍርሶ ወደ ፌዴራል ኃይሎች ለመቀላቀል ያሳለፈው ውሳኔ፣ ሕዝባዊ ዐመፅ መቀስቀሱን በዘግባው አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ላለፉት 60 ዓመታት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን የገለጸው የርዳታ ቡድኑ በአወጣው መግለጫ፣ ቹል ቶንጊክ የተባለው የጸጥታ መኰንኑና አማረ ክንደያ የተባለ አሽከርካሪ፣ እሑድ ዕለት ወደ ዐዲስ አበባ በመመለስ ላይ እያሉ “በጥይት ተመተው ተገድለዋል” ያለ ሲኾን፣ ስለ ግድያው ዝርዝር መረጃ አለመኖሩን ገልጿል።

በጉዳዩ አሳሳቢነት ምክንያት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሦስት የሰብአዊ ርዳታ ሓላፊዎች ለአሶሽየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፣ ግድያው የተፈጸመው፥ ባለፈው እሑድ፣ በቆቦ ከተማ አቅራቢያ፣ በፌዴራሉ የመከላከያ ሠራዊት እና በአማራ ክልል ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ነው።

"የድንጋጤያችንና የኀዘናችንን ጥልቀት መለካት አዳጋች ነው፤ በዚኽ ትርጉም የለሽ ጥቃት ተበሳጭተናል፤” ያሉት፣ የካቶሊክ ርዳታ አገልግሎት የኢትዮጵያ ወኪል አቶ ዘመዴ ዘውዴ፣ “የካቶሊክ የርዳታ ተቋም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ተጋላጭ የኾኑ ማኅበረሰቦችን ለማገልገል የሚሠራ የሰብአዊ ረድኤት ተቋም ነው፤”ብለዋል። ወኪሉ አክለውም፣ በሠራተኞቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ የርዳታ ተቋሙን ከአገልግሎቱ እንደማያግደው በመጥቀስ፣ “ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፋችንን ለመቀጠል ቁርጠኝነታችንን እንገልጻለን፤” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ፣ በልዩ ልዩ የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች እና የተኩስ ልውውጦች የተካሔዱ ሲኾን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ኹኔታው እስከ ሰኞ ድረስ መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል። አለመረጋጋቱ የተከሠተው፣ መንግሥት፥ “ለአገሪቱ የጸጥታ ስጋት ናቸው፤” ያላቸውን የክልል ኃይሎች ዳግም በማደራጀት “ጠንካራ እና የተማከለ ሰራዊት ለመገንባት” መወሰኑን ከአስታወቀ በኋላ ነው።

ዐዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ያወጣውና አሶሽየትድ ፕሬስ የተመለከተው የጸጥታ ማስጠንቀቂያ፥ በቆቦ፣ በወልዲያ እና በሰቆጣ አካባቢዎች፣ በአማራ ልዩ ኃይሎች እና በፌዴራል ሠራዊት መካከል፣ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ያካተተ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ገልጿል። የኤምባሲው ማስጠንቀቂያው አክሎም፣ በቆቦ ዙሪያ በተካሔደው የተኩስ ልውውጥ፣ የሰው ሕይወት ማለፉን አመልክቷል።

በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች ደግሞ፣ ተቃዋሚዎች፥ ጎማዎችን በጎዳናዎች ላይ በማቃጠል መንገድ የዘጉ ሲኾን፣ ይህም፣ በኢትዮጵያ ኹለተኛው ትልቁ ክልል እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉሏል። መንግሥትም፣ የሰዓት እላፊ እና የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመጣል፣ በበርካታ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በአማራ ክልል ሕዝባዊ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም፣ ፕሮግራሙን ማንኛውም ዋጋ በመክፈል ወደፊት እንደሚገፉበት፣ ባለፈው እሑድ ባስታወቁበት የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ ኾን ብለው አፍራሽ ሚና በሚጫወቱ አካላት ላይ የሕግ ማስከበር ርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ ክልሎች፥ ሕግንና ሥርዐትን ለማስከበር የፖሊስ ኃይል ማቋቋም እንደሚችሉ ቢደነግግም፣ አብዛኞቹ ክልሎች፣ ጠንካራ የጸጥታ ኃይሎችን ገንብተዋል። በመሬት እና በሀብት ክፍፍል ምክንያት በሚፈጠሩ አለመግባባቶች፣ በክልሎች አዋሳኞች በሚኖሩ ማኅበረሰቦች መሀከል የሚፈጠር ግጭት የተለመደ ሲኾን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የክልል ጸጥታ ኃይሎች የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ እንደጣሉት በማስታወሻቸው አስፍረዋል።

እ.አ.አ በ2020፣ በትግራይ በተቀሰቀሰው እና ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ በተፈረመ የሰላም ስምምነት በቆመው ጦርነት፣ የአማራ ክልል ኃይሎች ከፌዴራል ሠራዊቱ ጋራ ኾነው ከህወሓት ኃይሎች ጋራ በመዋጋት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

የፌዴራል መንግሥቱ፣ እ.አ.አ በ2021፣ ጦርነቱ ወደ ክልላቸው እንዳይስፋፋ መግታት ባለመቻሉና በኢትዮጵያ ትልቁ ክልል በኾነው የኦሮሚያ ክልል፣ ታጣቂዎች፥ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ባለማስቆሙ፣ በርካታ የአማራ ተወላጆች ዘንድ የመካድ ስሜት ይስተዋላል። የብሔሩ ተወላጆች፣ የክልላቸው ልዩ ኃይል ከፈረሰ፣ ምንም ዐይነት የጥበቃ ዋስትና እንደማያገኙም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል የፌደራል መንግሥት የክልል ኃይሎችን ለመበተን ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በአማራ ክልል እየተካሄዱ ስላሉ ተቃውሞዎች በጋዜጠኞች የተጠየቁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቬይዳንት ፓቴል በሰጡት ምላሽ፣ ስለጉዳዩ እንደማያውቁ እና እንደሚያጣሩ ገልፀው፣ ሆኖም በህዳር ወር ግጭት ለማቆም የተደረገውን ስምምነት ወደፊት ለስማቀጠል ህሉም ወገኖች ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG