በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ የቀረበባቸውን ክስ መቃወም ቀጥለዋል


ትረምፕ የቀረበባቸውን ክስ መቃወም ቀጥለዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:07 0:00

ትረምፕ የቀረበባቸውን ክስ መቃወም ቀጥለዋል

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የንግድ መዝገቦችን በማጭበርበር ተጠርጥረው በኒው ዮርክ ግዛት ለቀረበባቸው 34 የወንጀል ክሶች "ጥፋተኛ አይደለሁም" ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። ፍርድ ቤት ከቀረቡ ከሰዓታት በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግርም ክሱን ውድቅ አድርገው የኒው ዮርክ አቃቤ ህግን ዓላማ ተችተዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት በኒውዮርክ ከተማ ለሚገኘው ፍርድቤት እጃቸውን ሰጥተው፣ ከአንዲት የወሲብ ፊልሞች ላይ የምትተውን ሴት ጋር ጨምሮ የነበራቸውን ያልተገቡ ፆታዊ ግንኙነቶች ለመደበቅ የንግድ ሰነዶችን አጭበርብረዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ተቃውመዋል።

የማንሃታን አውራጃ አቃቤ ህግ አልቪን ብራግ ክሱን ሲያብራሩ "ሌሎች ወንጀሎችን ለመሸፈን ሰላሳ አራት ሀሰተኛ ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል። ግለሰቡ ማንም ቢሆን፣ እነዚህ በኒውዮርክ ግዛት ከባድ ወንጀሎች ናቸው" ብለዋል

ትረምፕ ከፍርድ ቤት ቆይታቸው በኋላ ወደሚኖሩበት ፍሎሪዳ ግዛት ሲመለሱ በደጋፊዎቻቸው አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን የግል ንብረታቸው በሆነው ማር-አ-ላጎ ሪዞርት ባደረጉት እና በቴሌቭዥን በተላለፈው ንግግራቸው "አቃቤ ህጉ የፖለቲካ ዓላማ አላቸው"ብለዋል።

"በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ አንድ ያልተሳካለት የአውራጃ አቃቤ ህግ የቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዝዳንትን፣ ሁሉም ባለሞያ እና የህግ ተንታኝ የሚያስከስስ ነገር እንደሌለ እየተናገረ፣ ክስ መስርቷል። ምንም የሚያስከስስ ጉዳይ የለም" ብለዋል።

"እንደዚህ ዓይነት ነገር በአሜሪካ ይከሰታል ብዬ አስቤ አላውቅም" ያሉት ትረምፕ አክለው "የሠራሁት ብቸኛው ወንጀል ሀገራችንን ሊያጠፏት ከሚፈልጉ ሰዎች ያለፍርሃት መከላከል ነው" ብለዋል።

ትረምፕ በማንሃታን አውራጃ አቃቤ ህግ ቢሮ ክስ የቀረበባቸው እ.አ.አ በ2024 በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ለመግባት መሆኑንም ጠቁመዋል። ከህዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት፣ ትራምፕ በሚቀጥለው ዓመት ለሚደረገው ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ ወክለው ለመወዳደር የቀረቡ እጩዎችን በሙሉ በልጠው እየመሩ ነው።

ከሕዝብ የተውጣጡ ዳኞች ግን ትረምፕ መከሰስ አለባቸው ሲሉ ድምፅ የሰጡ ሲሆን በጆርጅ ታውን ዩንቨርስቲ የህግ መምህር ፓውል ሺፍ በርማን በህግ ሂደቱ ላይ እያደረሱት ያለው ጥቃት እራሳቸው ላይ መዘዝ ያመጣባቸዋል ይላሉ።

"ክሱ የሚሰማው በመረጃ እና በህጉ ላይ ተመስርቶ ነው። እና ደግሞ ይሄ ከአሜሪካ ህዝብ ጋር ለሚኖራቸው ግንኙነት አይረዳቸውም፣ ምክንያቱም አሜሪካውያን የቀድሞ ፕሬዚዳንቱን በተመለከተም ቢሆን፣ የህግ ሂደቱ የተሟላ እና ፍትሃዊ ሆኖ ሲሠራ ማየት ይፈልጋሉ።"

ኒውዮርክ ከሚገኘው ፍርድ ቤት ውጪ የተሰብሰቡ ሰዎች የተከፋፈሉ እና ስሜታዊ ነበሩ። ዲዮን ቺኒ ለምሳሌ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ደጋፊ ሲሆን "ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕን እደግፋለሁ። እሳቸው በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ታላቁ ፕሬዚዳንት ናቸው፣ ምናልባትም በምድር ፕላኔት ላይ ያልታየ ምርጥ መሪ" ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።


ጀነፈር ፊሸር ደግሞ በተቃራኒው የትረምፕ ደጋፊ አይደለችም። "እሳቸው አታላይ ናቸው" የምትለው ፊሸር "አሁንም ድረስ የተታለሉ ብዙ ሰዎች አሉ። የኒው ዮርክ ነዋሪዎችን ግን አያታልሉም። ነገር ግን ብርሃኑን ማየት እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች።

ትረምፕ ፍርድ ቤት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን በሰጡበት ወቅት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዋይት ኃውስ መደበኛ ሥራቸውን ማከናወናቸውን ቀጥለዋል። ባይደን በወቅቱ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አማካሪዎቻቸው ጋር ተገናኝተው ሰው ሰራሽ ልኅቀት ስላለው ጥቅም እና ጉዳት አስተያየታቸው ሲሰጡ ነበር። ስለዶናልድ ትራምፕ ክስ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸውን ጥያቄም ችላ ብለዋል።

የሴኔቱ አብላጫ ድምጽ መሪ ቸክ ሹመር በበኩላቸው ባወጡት መግለጫ ትረምፕ የንግድ ሰነዶችን በማጭበርበር ለቀረበባቸው 34 የወንጀል ክሶች ፍትሃዊ ፍርድ ያገኛሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

በርካታ የሪፐብሊካን ህግ አውጪዎች ግን ይህን አመለካከት አይጋሩም። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ላይ የቀረበው ክስ ፖለቲካው ይዘት ፓለቲካዊ ይዘት ያለው ነው የሚል አቋም አላቸው።

XS
SM
MD
LG