በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ትረምፕ ለችሎት ፍልሚያው ተዘጋጅተዋል”- ጠበቃቸው


“ትረምፕ ለችሎት ፍልሚያው ተዘጋጅተዋል”- ጠበቃቸው
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:53 0:00

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣ የወሲብ ፊልም ተዋናዪቱን ዝም ለማሰኘት መደለያ ከፍለዋል፤ በሚል እንዲከሠሱ የተላለፈባቸውን የሕግ ውሳኔ ለመፋለም ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

ትረምፕ ለሚጠብቃቸው የወንጀል ክሥ ሒደት፣ ከችሎት ፊት ለመቅረብ፣ ነገ ማክሰኞ፣ ወደ ፍርድ ቤት ለማምራት መዘጋጀታቸውን ጠበቃቸውም አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ጠበቃ ጆ ታኮፒና፣ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ የተከሠሱት ትረምፕ፣ በሕግ ሒደቱ ፍርድ ቤት ስለ መቅረባቸው ምን እየተሰማቸው እንደኾነ በኤቢሲ ቴሌቪዥን ላይ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ “እኔ ተስፋ የማደርገው፣ እዚያ ቶሎ ገብተን ቶሎ መውጣት እንድችል ነው፡፡ ያው እንደተለመደው፣ ከዳኛው ፊት ቀርበን፣ ጥፋተኛ አይደለንም፤ እንላለን፡፡ ተቃውሟችንን የምናሰማበትን የጊዜ ሰሌዳ እናወጣለን፤ ሌሎች ነገሮች ወይም ግኝቶች ቢኖሩ ወደፊት እንቀጥላለን፡፡” ብለዋል፡፡

የክሡ ዝርዝር፣ ገና አልተገለጸም፡፡ የሕግ ባለሞያዎች ግን፣ ከወሲብ ፊልም ተዋናዪቱ ስቶርሚ ዳንኤል ጋራ በተደረገው ስምምነት እና በንግድ ሰነዶች ማጭበርበር ዙሪያ ሊያተኩሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

የትረምፕ ጠበቃ፣ የክሥ ጭብጡ ደካማ እና ፖለቲካዊ መግፍኤ ያለበት ነው፤ ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡ ይኹን እንጂ፣ ክሡን የሚመለከቱት ዳኛ ገለልተኛ አይደሉም፤ የሚለውን የትራምፕ ስጋት አልተጋሩም፡፡

“ዳኛው ወገንተኛ ናቸው ብዬ አስባለኹ? በጭራሽ አላስብም፡፡ ገና በጉዳዩ ያላየኹትን ዳኛ፣ ከወዲሁ አድሏዊ ነው ብዬ እንዳስብ የሚያደርገኝ ነገር እንደምን ይኖራል?” ብለው ጠይቀዋል ጠበቃው፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት፣ ክሡን ስለመሠረቱት ዐቃቤ ሕግ አልቪን ብራግ፣ ጠንካራ ትችት አሰምተዋል፡፡ “ሚት ዘ ፕሬስ” በተሰኘው ፕሮግራሙ፣ ኤንቢሲ ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው የቀድሞው የማንሃተን አውራጃ ዐቃቤ ሕግ ሳይረስ ቫንስ፣ ያ የትረምፕ ንግግር፣ “ችግር ሊያስከትል ይችላል፤” በማለት ጣጠኛነቱን ገልጿል።

"በመንግሥት ሥራ ጣልቃ መግባት ወይም በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ ማስፈራራት የመሳሰሉት እንደዚኽ ዐይነት ክሦች ሲጨመሩና በዳኞቹ ፊት ስታቀርባቸው ፣ ዳኞቹ፣ ጉዳዩን የሚመዝኑበትን ክብደት ሊለወጠው ይችላል፤” ሲሉ ቫንስ ተናግረዋል፡፡

ትረምፕ ስለ ገጠሟቸው፣ ስለ አኹኑም ኾነ ስለ ሌሎቹ የወንጀል ክሦች በአደባባይ እንዳይናገሩ ዳኛው ሊከለክሏቸው ይችላሉ፤ ተብሎ እንደማይጠበቅ፣ በምስጢራዊ ሰነዶች ዙሪያ ጠበቃቸው የኾኑት ጂም ትረስቲ፣ ፎክስ ኒውስ ቴሌቭዥን ላይ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ትረስቲ፣ ስለ ንግግሩ መዘዝ አያይዘው ሲናገሩ፣ “ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩትን ሰው፣ በፍርድ ቤት ስለ ተያዘ ጉዳይ እንዳይናገሩ ለማዘዝ፣ ለዳኛው በጣም አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ በዚኽ አገር ላይ ስለሚያስከትለው ትልቅ ተጽእኖ ነው እየተናገርኹ ያለኹት፤” ብለዋል፡፡

የትረምፕ ጠበቆች ከወዲሁ እንዳሳወቁት፣ 45ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት፣ ነገ ማክሰኞ፣ በይፋ የተመሠረተባቸውን ክሥ በትክክለኛ ይዘቱ ከማንበባቸው በፊት፣ የጣት አሻራቸውን ሲሰጡና ፎቶግራፍ ሲነሡ፣ የደኅንነት ጠባቂዎቻቸው በፍርድ ቤቱ አካባቢ ያለውን የጸጥታ ኹኔታ ጥብቅ ያደርጋሉ፡፡

ዶናልድ ትረምፕ፣ ማክሰኞ ምሽቱን፣ ፍሎሪዳ ግዛት ማር አላ ጎ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ንግግር ያደርጋሉ፤ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጽ/ቤታቸው አስታውቋል፡፡

ትረምፕ ከወሲብ ተዋናዪቱ ጋራ በተገናኘ ለችሎት ፍልሚያ ያደረሳቸው ጉዳይ ዳግም ጉልሕ የኾነው፣ እአአ በ2024 ለሚካሔደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር እየተሰናዱ ባሉበት ወቅት ነው፡፡

XS
SM
MD
LG