ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 25/2015 ዓ.ም ከቀትር በኋላ የኒው ዮርክ ክፍለ ግዛት ማንሃታን በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡት የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ፤ የቀረቡባቸውን 34 የወንጀል ክሶች በሙሉ እንዳልፈፀሙ ገልፀው "ጥፋተኛ አይደለኹም"ሲሉ ክሱን አስተባብለዋል።
ትረምፕ ፍርድ ቤት የቀረቡት ስቶርሚ ዳኒየልስ ከተባለች የወሲብ ፊልም ተዋናዪት ጋራ የነበራቸው ግንኙነት አደባባይ እንዳይወጣ ለማፈን “ለጥብቅና ጉዳዮች የዋለ” በሚል 130 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር መደለያ ከፍለዋል በሚል ክሥ ስለቀረበባቸው ነው።
ትረምፕ ስቶርሚ ዳኒየልስ "አንድ ቀን ግንኙነት ፈጽመናል" ያለችውን ሲያስተባብሉ ቆይተዋል። በወቅቱ ጠበቃቸው እና የፖለቲካ ጉዳዮች አመቻቻቸው የነበሩት ማይክል ኮኸን ለስቶርሚ ዳኒየልስ ገንዘቡን መክፈላቸውን እና ገንዘቡ በትረምፕ ድርጅት የሕግ ጉዳዮች ወጪነት ተመዝግቦ የተመለሰላቸው መሆኑን ግን አላስተባበሉም። ትረምፕ በድርጅታቸው የተመዘገበው ከሰባት ዓመታት በፊት የነበረ የሕግ ጉዳይ ወጪ እንደሆነ በመናገር ሲከራከሩ ቆይተዋል።
የሰባ ስድስት ዓመቱ ትረምፕ ፕሬዚደንት ከመኾናቸው በፊት ለብዙ አስርት ዓመታት ባለብዙ ህንጻ፣ ባለሀብት እና ተራ ወሬ የበዛበት እና የተብለጨለጨ ማኅበራዊ ህይወት በያዘው ስመ ጥር ስማቸው ታውቀው በኖሩባት በኒው ዮርክ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በወንጀል ክስ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ትረምፕ በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ የወንጀል ዶሴ የተከፈተበት የመጀመሪያው መሪ ቢሆኑም ለመጪው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሪፖብሊካን ፓርቲው አባላት ሰፊ ድጋፍ ያላቸው ቀዳሚ ተፎካካሪ ናቸው።
የቀድሞው ፕሬዚደንት የክስ ክህደት ቃላቸውን የሰጡት ኒው ዮርክ ክፍለ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ዳኛ ሁአን መርቻን ፊት ፊት ቀርበው ሲሆን ዳኛው የክሥ ሂደቱ በብዙኃን መገናኛ እንዳይተላለፍ ክልከላ በማድረጋቸውየዜና ማሰራጫዎች በቀጥታ የክስ ሂደቱን ለማስተላለፍ አልቻሉም።
ትረምፕ ችሎቱ ፊት ከመቅረባቸው አስቀድሞ እንደማናቸውም በወንጀል ድርጊት ተከሳሽ ተመዝግበው አሻራቸው ተወስዷል። በካቴና ታስረው እንዲገቡ ያልተደረገው የቀድሞ ፕሬዚደንት መኾናቸው ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ባለሥልጣናት አስረድተዋል። የተከሳሽ ፎቶግራፍ አንስተዋቸው እንደሆንም ለጊዜው አልታወቀም።
በፍርድ ቤቱ እና ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኘው እና የቀድሞው ፕሬዚደንት ትናንት ሰኞ ከፍሎሪዳ ተጉዘው ባደሩበት ኒው ዮርክ ማንሃታን ከሚገኘው የግል ሕንፃቸው “ትረምፕ ታወር” ዙሪያ ብዛት ያላቸው የጸጥታ ጠባቂዎች ተሰማርተዋል። ትረምፕ ማታውን ከጠበቆቻቸው ጋራ ሲማከሩ እና የሚስጥራዊ ደህንነት አገልግሎት አባላቱም ዛሬ ከህንጻው ወጥተው ወደ ፍርድ ቤቱ ችሎት የሚገቡበትን መንገድ ሲያዘጋጁ አምሽተዋል።
ዛሬ በርካታ ሰዎች የቀድሞው ፕሬዚደንት ከትረምፕ ህንጻ ሲወጡ እና ፍርድ ቤቱም ሲገቡ ለምመልከት ተሰባስበው የነበረ ሲሆን ከፍርድ ቤቱ ባሻገር በሚገኝ መናፈሻ ላይ የሳቸው ደጋፊዎች ከጥቂት ተቃዋሚዎች ጋር ተደባድበዋል።
(የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ አራሽ አራብሳዲ ያጠናቀረው ዘገባ ነው)
የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ " ኒውዮርክ መኖሪያችን እንጂ የናንተን ካለቦታው የሚሰነዘር ቁጣ ማራገፊያ ሜዳ አይደለችም ራሳችሁን ተቆጣጠሩ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዶናልድ ትረምፕ ከፍርድ ቤቱ ሂደት በኋላ ወደ ፍሎሪዳው መኖሪያቸው ወደማራላጎ ለመሄድ ወደ ወደኒው ዮርኩ ላጓርዲያ አውሮፕላን ጣቢያ የተጓዙ ሲሆን በማራላጎ ዛሬ ማታ ንግግር ለማድረግ እና ከደጋፊዎቻቸው ጋር ለመገናኘት ዕቅድ እንዳላቸው ተመልክቷል።