በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የ“ረቂቅ ሙዚቃ” ባለወንበር እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ስንብት


የፒያኖዋን እመቤት የሚያዘክሩ ሥራዎቻቸው፣ ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማገዝ አልሞ ከተቋቋመ ፋውንዴሽን ዌብሳይት ላይ የተገኘ።
የፒያኖዋን እመቤት የሚያዘክሩ ሥራዎቻቸው፣ ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማገዝ አልሞ ከተቋቋመ ፋውንዴሽን ዌብሳይት ላይ የተገኘ።

• “የጥሙና ምንጭ በኾነው የረቂቅ ሙዚቃ ኀልዮ እና ክወና በልዩነት ይታያሉ” - የሙዚቃ ባለሞያዎች

“የፒያኖዋ እመቤት”፥ በኢትዮጵያ ክላሲካል ሙዚቃ ዘርፍ ብቸኛዋ የሙዚቃ ቀማሪት እና ፒያኒስትነት እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ወይም ከምንኵስናቸው በፊት ይጠሩበት በነበረው ስማቸው የውብዳር ገብሩ፣ በ99 ዓመት ዕድሜያቸው፣ ሕይወታቸው በአለፈበት በኢየሩሳሌም ከተማ፣ ዐርብ፣ መጋቢት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ሥርዐተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።
ዘመን ተሻጋሪ ስም እና ሥራ አኑረው ያለፉትን፣ የእማሆይ ጽጌን አስተዋፅኦ ለመዘከር፣ ሀብታሙ ሥዩም፣ ወጣት የሙዚቃ ባለሞያዎችን አነጋግሮ ዘገባ አሰናድቷል።
የሙዚቃ ባለሞያዋ ፍሬ ሕይወት ውድነህ፣ ሙዚቃ፥ መምህር፥ አቀናባሪ እና ደራሲ ኢዮኤል መንግሥቱ እንዲሁም የሙዚቃ ባለሞያ፣ ለራዲዮ እና ለቴሌቭዥን የሙዚቃ ትርኢት አሰናጇ ብሌን ዮሴፍ፣ ሐሳባቸውን ያካፈሉን እንግዶች ናቸው።

የ300 “ረቂቅ ሙዚቃ” አበርክቶ

ለእማሆይ ጽጌ ማርያም፣ ፒያኖ የሙዚቃ መሣሪያ ብቻ አይደለም፡፡ የሕይወት ዘመን “ጓድ” እንጂ። ለዚያም ይመስላል፣ በቅርብ ሰዎቻቸው በተሰናዳው ዘጋቢ ፊልም ላይ፣ “ፒያኖ ከልጅነቴ ጀምሮ ጓዴ ነው፤. . . ከስምንት ዓመቴ ጀምሮ” ሲሉ መደመጣቸው።
ከአዳጊነት የሕይወት ምዕራፋቸው ጀምሮ ወዳጅ ያደረጉት ፒያኖ ታዲያ፣ የእርሳቸው “ጓድ” ብቻ ኾኖ አልቀረም። በዓመታት ውስጥ የብዙ ኢትዮጵያውያን የጽሙና እና የመልካም ትዝታ ምንጭም ኾኗል። ለሙዚቃ ባለሞያዋ ፍሬ ሕይወት ውድነህ እና ለሙዚቃ መምህሩ፣ አቀናባሪው እና ደራሲው ኢዮኤል መንግሥቱ፣ “The Homeless Wanderer - ቤት አልባ መንገደኛ” ሲሉ እማሆይ የሰየሙት ሥራ ልዩ ትርጉም አለው።

ለሌላኛው የሙዚቃ ባለሞያ፣ ለራዲዮ እና ቴሌቭዥን የሙዚቃ ትርኢት አሰናጇ ብሌን ዮሴፍ ደግሞ፣ “Mother's love - የእናት ፍቅር” ከልቧ የቀረ ሥራ ነው፡፡ "(ሙዚቃውን ሳዳምጥ) የጽሙና፣ የመረጋጋት፣ ነገሮችን በማስተዋል የመመርመር ዐይነት ስሜት ይመጣብኛል። የእውነትም ለእርሱ ታስበው የተቀመሩ ይመስለኛል እንደ ሙዚቃ መለስ ብዬ ሳያቸው፤” ትላለች ብሌን።
በቅርብ ዘመዶቻቸው አቆጣጠር፣ ከ300 በላይ ረቂቅ ሙዚቃን፣ ለአንድ ምእት ዓመት አንድ ፈሪ በኾነው የሕይወት ዘመናቸው ለአድማጮች አበርክተዋል፡፡ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡ የሙዚቃ ሞያተኞችን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያንን፣ ለነፍስ በሚጥሙ ረቂቅ ሙዚቃዎቻቸው ተመስጦ እና አገልግሎት የባጁት እማሆይ ጽጌ ማርያም፣ በሳምንቱ መጀመሪያ፣ ከዚኽ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የየውብ ዳር ጉልሕ ቀለማት

በ1916 ዓ.ም. ከአባታቸው ከንቲባ ገብሩ ደስታ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ካሳዬ የለምቱ፣ በዐዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት እማሆይ ጽጌ ማርያም፣ ከመመንኰሳቸው በፊት የተጽውኦ ስማቸው የውብዳር ገብሩ ነበር፡፡
በስድስት ዓመታቸው ወደ ስዊዘርላንድ ተልከው፣ ፒያኖ እና ቫዮሊን አጥንተዋል። በመዋዕለ ዘመናቸው፥ በዓለማዊው እና በመንፈሳዊው፣ በአገርኛው እና በአውሮፓውያኑ የሙዚቃ ዘይቤ ውስጥ ለማለፍ ዕድል ያገኙት እማሆይ፣ በኹለቱ ዓለማት መሀከል “ድልድይ” እንደኾኑ በሚነገርላቸው ሥራዎቻቸው፣ በኢትዮጵያ የ“ረቂቅ ሙዚቃ” ምዕራፍ ውስጥ ጉልሕ ቀለም ኾነዋል።

በ“ረቂቅ ሙዚቃ” ኀልዮ እና ክወና የእማሆይ ልዩነት

በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥባባት ኮሌጅ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት መምህር፣ የሙዚቃ አቀናባሪ እና ደራሲ የኾነው ኢዮኤል መንግሥቱ፣ የእማሆይ ጽጌ ማርያም የሙዚቃ ዘርፍ አስተዋፅኦ ሲያወሳ፣ “የረቂቅ ሙዚቃ ኀልዮ እና ክወና ብዙም በማይታወቅበት የእርሳቸው ዘመን[ላደረጉት ነገር] ትልቅ ስፍራ እሰጣቸዋለኹ። . . . የኢትዮጵያን ቅኝት፣ የዜማ አካሔድ፣ ጌጣጌጥ፣ ላህይ(ቃና) ተጠቅመው፣ ከአውሮፓ ሙዚቃ ጋራ የአዋሐዱበት መንገድ፣ እርሳቸውን በልዩነት እንድመለከታቸው ያደርገኛል፤” ይላል። ኢዩኤል አክሎም፣ ሥራቸውን በቀደመው ዘመን ለማስቀረፅ መቻላቸው፣ የኢትዮጵያ “ረቂቅ ሙዚቃ”፣ በዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ ለማስቻል ማገዙን ይናገራል።

በአዳጊነት ዘመናቸው፥ እስርን፣ ከሀገር ከወገን መራቅን የመሰሉ አስከፊ የሕይወት ገጠመኞችን የተጋፈጡት እማሆይ ጽጌ ማርያም፣ ብዙም ባልተስፋፋው የኢትዮጵያ የ“ረቂቅ ሙዚቃ” ዘርፍ፣ ለዓመታት ጎልተው የታዩ እንስት ከያኒ ነበሩ። “ፒያኖ፥ ብዙ ጥሙና፣ ርጋታ፣ ትዕግሥት፣ ዝግታ እና ጸጥታ ይሻል፡፡ ለብዙ ሰዓታት አንድ ነገር ላይ ማተኮርንና መቀመጥን ይጠይቃል፤” የምትለው የሙዚቃ ባለሞያዋ፣ የራዲዮ እና የቴሌቪዥን የሙዚቃ ትርኢት አሰናጇ ብሌን ዮሴፍ፣ እማሆይ፥ ድርብርብ የሞያ እና የሕይወት ምዕራፎችን አልፈው፣ በወጥ ድርሰት በዘርፉ ደምቀው መውጣታቸው፣ የጥንካሬ እና የጽናት ማሳያ አድርጋ በመውሰድ ታደንቃለች፡፡ አያይዛም፣ “ለሙዚቀኛው፥ የትጋት ምሳሌ፣ ከሙዚቃው ውጭም ላለው፥ በትዕግሥት እና በጥሞና አንድን ነገር ማሳካት እንደሚቻል አርኣያ መኾን የሚችሉ ናቸው፤” በማለት ታብራራለች፡፡

የወንበሩ አደራ ተቀባይ እና ወራሽ እንዴት?

ፍሬ ሕይወት ውድነት፣ በሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገራት መድረኮች ላይ በመሣሪያ የተቀነባበሩ ሙዚቃዎች ከዋኝ እና የረቂቅ ሙዚቃዎች ተጨዋች ናት፤ የሙዚቃ መምህርትም ናት።
የእማሆይ ጽጌ ማርያም፣ ከፍተኛ እና ልዩ አበርክቶ በቅጡ አለመወሳቱን የምትናገረው ፍሬ ሕይወት፣ ሥራቸው ለቀጣይ ትውልድ የ“ረቂቅ ሙዚቃ” ባለሞያዎች እንዲሸጋገር ጥረት ሊደረግ እንደሚገባው ትናገራለች። “የእርሳቸውን ሙዚቃ፣ ማንኛውም ሰው አንብቦ እንዲጫወተው በኖታ(በዜማ ትእምርት) ተጽፎ ሊቀመጥ ይገባል። [በርግጥ]የተጻፉ ቢኖሩም፣ በብዛት አይገኙም፤ እንደ ልብ ቢያገኙት ቢደረግ፤” በማለት ትመክራለች፡፡

በኢትዮጵያ የ“ረቂቅ ሙዚቃ” ወንበር እመቤት ኾነው ከሰፈኑት እማሆይ ጽጌ ማርያም በኋላ፣ ተናገር በከንፈሬ ተቀመጥ በወንበሬ ለመባል የሚበቃን የወንበሩን አደራ ተቀባይ እና ወራሽ እንዴት እንፍጠር ብሎ ማሰብ አይቀሬ ይመስላል፡፡ መምህር፣ የሙዚቃ አቀናባሪ እና ደራሲው ኢዮኤል መንግሥቱ፥ ዘርፉን ከልብ ባለመረዳት የመነጨ፣ የትኩረት ማጣት ፈተናዎች ሊታሰብባቸው እንደሚገባ መክሯል።

የ“ረቂቅ ሙዚቃ” ባለወንበር እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ስንብት
please wait

No media source currently available

0:00 0:16:17 0:00

“የፒያኖዋ እመቤት” ኑዛዜ እና ፋውንዴሽን

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት፣ የፒያኖዋን እመቤት የሚያዘክሩ ሥራዎቻቸው፣ ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማገዝ ያለመ ፋውንዴሽን ተቋቁሟል። ፋውንዴሽኑ፣ በተለይ በረቂቅ የሙዚቃ ዘርፍ፣ ተምሳሌት ለሚሹ ወጣቶች ፋይዳ ያላቸው ሥራዎችን ለመሥራት ተሰናድቷል። በኅልፈታቸው ማግሥት ያነጋገርናቸው፣ የፋውንዴሽኑ አጋር መሥራች፣ የእማሆይ የእኅት ልጅ ሐና ከበደ፣ በእማሆይ ላይ የሚያተኩር ዘጋቢ ፊልም እና መጽሐፍን ይፋ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ለመከወን መታቀዱን ነግረውናል።
በ21 ዓመታቸው፣ ከዓለማዊው አኗኗር በመለየት ከመነኑ በኋላ፣ ተሰጥኦዋቸውን፣ ለበርካቶች የጥልቅ ጥሙና እና የደግነት ምንጭ ያደረጉት እማሆይ ጽጌ ማርያም፣ በመጨረሻው የዕድሜያቸው ምዕራፍ ላይም ኾነው፣ ለቀጣዩ ትውልድ ደግነትን ትተዋል፤ ለዓመታት ሲጠቀሙበት የነበረውን ፒያኖ፣ ለያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲሰጥ ተናዝዘዋል።

“ሥጋዬ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጣ”

በአሳለፍነው እሑድ፣ ለ40 ዓመት ገደማ በኖሩባት እስራኤል - ኢየሩሳሌም ከተማ፣ ከዚኽ ዓለም በሞት የተለዩት እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ፣ ሥርዐተ ቀብራቸውም በቃላቸው መሠረት በዚያው ተፈጽሟል።
ሞት የዓለመ ሥጋ የሕይወት ዘመን መቋጫ ነው። ስማቸው፥ ከኅልፈታቸው ወዲያም ሕያው ኾኖ ስለ መዝለቁ፣ ለዚኽ ዘገባ ሐሳባቸውን ያካፈሉን የዐዲሱ ትውልድ ባለሞያዎችን ጨምሮ በርካታ አድናቂዎቻቸው እና ተከታታዮቻቸው በመመስከር ላይ ይገኛሉ፡፡

XS
SM
MD
LG