ሃገር ሰላም እንድትሆን እና ጤናማ የሆነ ማኅበረሰብ ለማፍራት በወጣቶች እና ጎልማሶች ብሎም በአዛውንቶች መሃከል መተጋገዝ እና መደጋገፍ ያስፈልጋል፡፡ የዘንድሮ አለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ለ22ኛ ጊዜ ‘የትውልድ ቅብብሎሽ ለሁሉም የሚመች አለምን ለመፍጠር’ በሚል መሪ ቃል በአለም ዙሪያ ታስቧል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ19ኛ ጊዜ "በትውልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያ ትጸናለች” በሚል መሪ ቃል ታስቧል፡፡
ከአርባ በላይ አረጋዊያንን በመደገፍ የሚታወቀው ወጣት ዘካሪያስ ኪሮስ ለሃገራቸው የሰሩ አረጋዊያን በመደገፍ ውስጥ እሱና ሌሎች በጎ ፍቃደኞች ጓደኞቹ ከመንፈሳዊ እርካታ ጀምሮ፣ የሃገር እና የቤተሰብ ፍቅርን ማዳበራቸውን ይናገራል፡፡ በሌላ በኩል ከጋቢና ቪኦኤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የስድስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ከበደ ቦጋለ ልጆችን እኛ ሰርተን እና ሆነን ሳናሳያቸው ውጤት መጠበቅ የለብንም ይላሉ፡፡
የትውልድ ቅብብሎሽ በመደጋገፍ ውስጥ እንደሚገኝ የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሞያ አቶ ግርማ ከበደ ይናገራሉ፡፡ ‘’ወጣቶች ልጅነትን አልፈው ነው ወጣትነት ላይ የሚድረሱት” የሚሉት ባለሞያው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በቂ ጊዜ በማሳለፍ ባህል እና ትውፊትን ማጋራት እንዲሁም በዘመናት ውስጥ የሚመጡ የአስተሳሰብ እና የአኗኗር ለውጦችን መቀበል አለባቸው ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት በፖሊሲው ውስጥ ታዳጊዎች በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እንዲሳተፉ ማመቻቸት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
/ዝርዝሩን ከተያያዘው የምስል ፋይል ይከታተሉ/