በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተፈፀመ የተባለውን አሰቃቂ ግድያ የሚመረምር ቡድን ወደ ስፍራው አቅንቶ ሥራ መጀመሩ ተገለጸ


ፎቶ፦ የፍትህ ሚኒስቴር የፕሬስ ሴክሬቴሪያት አቶ አወል ሱልጣን በቢሮአቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ። ከማኅበራዊ ገፃቸው ላይ የተገኘ።
ፎቶ፦ የፍትህ ሚኒስቴር የፕሬስ ሴክሬቴሪያት አቶ አወል ሱልጣን በቢሮአቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ። ከማኅበራዊ ገፃቸው ላይ የተገኘ።

ከፍትህ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ፖሊስ የተውጣጡ አባላትን ያካተተ የወንጀል ምርመራ ቡድን፣ የምርመራ ስራውን እያከናወነ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አንድ በሕይወት የነበረን ሰው ቀድመው ከተገደሉ ሰዎች አስከሬን ጋር የማቃጠል ድርጊት በመንግሥት የፀጥታ አባላትና ሌሎችም ሰዎች ተሳትፎ መፈጸሙን እንዳረጋገጠ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በጉባ ወረዳ በምትገኘው አይሲድ ቀበሌ፣ በሕይወት የነበረን አንድ ግለሰብ ከአስከሬኖች ጋር አቃጥሎ በመግደል ሰሞኑን የተፈጸመውን አሰቃቂ የግድያ ወንጀል የሚመረምር ቡድን፣ ድርጊቱ ወደ ተፈጸመበት ስፍራ ባለፈው ረቡዕ አቅንቶ ስራ መጀመሩን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ስለ ምርመራ ቡድኑ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራሪያ የሰጡት የፍትህ ሚኒስቴር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን

በአጠቃላይ 8 አባላትን ያካተተው ቡድኑ ምርመራውን በምን ያህል ጊዜ እንደሚያጠናቅቅ ተጠይቀው፤ “ለጊዜው በዚህን ያህል ጊዜ እናጠናቅቃለን ባንልም እጅግ ባጠረ ጊዜ ግን እናጠናቅቃለን” ብለዋል።

ከሁለቱ የፌዴራል ተቋማት ጠተውጣጡ አባላትን ካካተተው የምርመራ ቡድን በተጨማሪ፣ የቤኒሸንጉል ጉሙዝ ክልል አቃቤያን ህጎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በወንጀል ምርመራ ስራው ድጋፍ እንደሚያደርጉም የፍትህ ሚኒስቴር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የግድያ ድርጊቱን ማጣራቱን ገልጾ መጋቢት 4/ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ድርጊቱ ከተፈጸመበት አንድ ቀን በፊት ቢያንስ በ 20 የመንግሥት ፀጥታ አባላት እና በሲቪል ሰዎች ላይ በታጣቂዎች የተፈጸመው ግድያ ለዚህ ክስተት መነሻ መሆኑን አረጋግጫለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡

ግድያውን ከፈጸሙት ታጣቂዎች ጋር በተባባሪነት የተጠረጠሩ 8 የትግራይ እና 2 የጉሙዝ ተወላጆች በድምሩ 10 ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በጥይት እንደተገደሉ እና ሌላ አንድ ግለሰብ ደግሞ ከእነ ሕይወቱ ከ10ሩ ጋር እንዲቃጠልመደረጉን ኢሰመኮ አመልክቷል፡፡

በስፍራው የነበሩ የጸጥታ ኃይሎች በድርጊቱ የነበራቸው ተሳትፎ በተጨማሪ የወንጀል ምርመራ ሊጣራ እንደሚገባም ኢሰመኮ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ የትግራይ ክልልን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል፣ ወንጀለኞቹን ተጠያቂ ለማድረግ እንሰራለን ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡

መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችና በርካታ ተመልካቾች በተሰበሰቡበት አንድ በሕይወት የነበረ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ እሳት ውስጥ ሲጨመርና ከአስክሬኖች ጋር ሲቃጠል የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ ሚድያዎች መሰራጨቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙኒኬሽን በማግስቱ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን አውግዟል፡፡

በመግለጫው “መነሻቸውም ሆነ ማንነታቸዉ ምንም ይሁን ምን መንግስት ይህን አይነት ፍፁም ከሰብዓዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል” ማለቱም የሚታወስ ነው፡፡

ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG