በየዓመቱ የዲሞክራሲና ነፃነት አካሄድ በተመለከተ ጥናት የሚያካሄደው ብዱን ፍሪደም ሃውስ፣ በዚህ ሳምንት የዓለም ነፃነት ሪፓርቱን ይፋ አድርጓል። ቡድኑ ዲሞክራሲን፤ የፖለቲካ ነፃንትንና የሰብአዊ መብት አያያዝን በሚመለከት ጥናት ያካሄዳል። የዚህ ዓመት ሪፖርቱ በ210 አገሮችና አካባቢዎች ዉስጥ ያሉትን የፓለቲካ መብቶችና የህዝብ ነፃነቶችን አጥንቶና አመዛዝኖ በየዓመቱ በጥር ወር ይፋ የሚሆን ዘገባ ነዉ።
ዓመታዊው ዘገባ በአለም ደረጃ ነፃነት የቀነሰበትን ምክንያት ጠቅሶ፣ አምባገነን መንግስታት የከፋ የጭኮና ስልት በመጠቀማቸው፣ አሸባሪዎች ጥቃት በተከታታይ በፈጸሙት ሁነት እና የኢኮኖሚ ይዘት በአለም ደረጃ በማሽቆልቆሉ ነው ይላል።
በፍሪደም ሃውስ የነፃነትና የፕሬስ ጥናት ዳይረክተር ጀነፈር ደንሃም ኢትዮጵያን በተመለከተ፣ "ኢትዮጵያን በተመለከተ ቁጥራቸዉ አነስተኛ የሆነ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቢኖሩም አገሪቱ በጣም የረቀቁ ዘዴዎችን በመጠቀም በኢንተርኔት እና በድረ ገጽ ላይ የሚደረጉ የህዝብ የሃሳብ መለዋወጦችን ትከታተላለች። እናም በዚያ መንገድ ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ ትወስዳለች። ጦማሪያን፣ የኢንተርኔት ጋዜጠኞች እና የመሳሰሉት ኢላማ ናቸዉ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ናቸዉ፥ ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ከእስር ቢፈቱም እስራቱን ተከትሎ የሚደርስባቸዉ ጫና ቀጥሏል። ስለዚህ በአገሪቱ ዉስጥ ምንም የተለየ ሃሳብ ወይም ተቃዉሞ እንዳይሰማ ጥብቅ ቁጥጥር አለ" ብለዋል።
ዋና ጽ/ቤቱ ዩናይትድ ስቴትስ የሆነው የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ድርጅት ባለፈው ወር ባበቃው እአአ 2015 ዓ.ም. ነፃነት በአለም ደረጃ የቀነሰበት ዓመት ነበር ብሏል። ይህም ሁኔታ በተከታታይ ለአስር ዓመት ያህል እንደቀነሰ ቡድኑ ጨምሮ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥስት በኦሮምያ ክልል በተቀሰቀሱ ሰልፎች ላይ የወሰደውን እርምጃ በማስመልከት የዓለም ኅብረተሰብንና የአሜሪካ መንግሥስት መልስ አስመልክተው ጀነፈር፣ "በአህጉሪቱ ዉስጥ ይሁን ከአጉሪቱ ዉጪ ባሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች አመለካከት ዩናትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ መንግሥስት የምታሳየዉ ድጋፍ በጣም አሳዛኝ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግሥስት ለሚፈጽማቸዉ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂ አያደርጉትም በጭፍን ይደግፉታል። የኢትዮጵያ መንግሥስት የሚፈጽማቸዉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በብዙ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ተጠናቅረዉ ይፋ እየሆኑ ነዉ። የኢትዮጵያን መንግሥስት ስታወድስ መስማት ታዲያ በጣም አሳዛኝ ነዉ" ብለዋል።
ዓመታዊው የፍሪደም ሃውስ ዘገባ እንደሚያመለክተው ባለፈው ዓመት ብቻ በ72 ሃገሮች የአጠቃላይ ነፃነት ሁኔታ ቀንሷል። የነፃነት ማሽቆልቆል ከተጀመረባቸው ዓመታትም የከፋው አምና እንደሆነም ዘገባው አክሏል።
ጥናት ከተደረገባቸው 195 ሀገሮች 50ዎቹ ነፃ አይደሉም። 59ኙ ደግሞ በከፊሉ ነፃ ተብለዋል። የከፋ ጭቆና ያለባቸው ሀገራት ሶርያ፣ የቻይናው ቲቤት ራስ ገዝ ክልል፣ ሶማልያ፣ ሰሜን ኮርያ፣ ኡዝቤኪስታንና ኤርትራ እንደሆኑ የፍሪደም ሃውሱ ዘገባ ይገልጻል።
በተለይም ይላሉ ጀነፈር፣ በኤርትራና በሶማልያ ሁኔታ፣ "የመጥፎ መጥፎ የሚለዉ ዝርዝር ከ210 አገሮችና አካባቢዎች መካከል የመጨረሻዎቹ የከፋ የሰብአዊ መብት አያያዝ ያላቸዉ አስር አገሮች ዝርዝር ነዉ። ስለዚህ በአፍሪቃ ቀንድ ኤርትራና ሶማሊያ ከእነዚህ መሃል ናቸዉ። ያ ማለትም የፖለቲካና የሲቪል መብት አያያዝ ጭራሽ አዝቅጦ ዜጎች የሚመሯቸዉን መንግሥስት ሆነ የኑሯቸዉን ሁኔታ ለመወሰን ምንም መብት የላቸዉም። ኤርትራ ዉስጥ መንግሥስት ለመተቸት ብቻ ሳይሆን፣ የግል አመለካከታቸዉን ለመተንፈስ፥ በሚመርጡት ሞያ ለመስራትና የመሳሰሉት መብት የላቸዉም ማለት ነዉ።"
አክለውም፣ "መጀመሪያ ነገር ቁጥራቸዉ እጅግ ብዙ የሆነ ኤርትራዉያን ናቸዉ አገር ለቀዉ የሚሸሹት። የፓለቲካ ጥገኝነት ፍለጋ ወደ አዉሮፓ አገሮች ከሚሰደዱት ብዙ ቡድኖች መሃል ናቸዉ ኤርትራዉያን። ስለዚህ አገሪቱ ዉስጥ ስላለዉ ሁኔታ ከእነርሱ መረጃ እናገኛለን። ባለፈዉ ሰኔ ወር ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የስብአዊ መብት ድርጅት ኤርትራ ዉስጥ ስላኡ እጅግ አሳሳቢ የመብት ጥሰቶች ሁኔታ ሁለገብ የሆነ ዘገባ አዉጥቷል። እነዚህ መረጃዎች እንዴት እንደተገኙም በዝርዝር ተጠቅሷል በሪፓርቱ። ስለዚህ እኛም ከሚሰደዱ ሰዎች ስለአገሪቱ ሁኔታ መረጃዎች እናገኛለን በተጨማሪም ህይወታቸዉን ለአደጋ አጋልጠዉ ከአገር እንደሚወጡና አዉሮፓም ከደረሱ በኋላ የሚደርስባቸዉ መንገላታት ሲታይ አገሪቱ ዉስጥ ምን ያህል ችግር እንዳለ ያሳያል" ይላሉ ጀነፈር።
ጀነፈር ደንሃም፣ ሲቪል ማኅበረሰብና ጋዜጠኞች በኢትዮጵያና በኤርትራ ዉስጥ እንዴት ይስሩ ለሚለዉ ጥያቄ፥ ምንም መንቀሳቀሻ ስለሌለ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። አክለውለውም፣ የዓለም መንግሥታት ችግር በሚኖርበት ጊዜ ጉዳዮችን በግልፅ መተቸት ካልፈለጉ፣ ፍሪደም ሃውስና ሌሎች ለሰብአዊ መብት የሚሟገቱ ድርጅቶች የኤርትራንም ሆነ የኢትዮጵያን መንግሥት ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጫና ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ሪፖርት፣ ቱርክሜኒስታን፣ ምዕራብ ሰሃራ፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ፣ ሱዳን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒና ሳዊዲ አሬብያም አስከፊ ጭቆና ካለባቸው ሀገሮች ዝርዝር ውስጥ ናቸው። መካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ ባለፈው ዓመት አስከፊ ጭቆና የታየባቸው ክፍሎች እንደነበሩ ዘገባው ዘርዝሯል። በሪፖርቱ ላይ የተካሄደውን የቪድዮ ዝርዝር ለመከታተል፣ ይህንን ፋይል ይጫኑ። የድምጽ ፋይሉንም በመጫን ዘገባውን ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5