የአማራ ክልል አለመረጋጋት ጣናን አስግቷል

Your browser doesn’t support HTML5

የአማራ ክልል አለመረጋጋት ጣናን አስግቷል

አማራ ክልል ውስጥ በቀጠለው አለመረጋጋት ምክንያት ጣና ላይ እምቦጭን የማስወገድ ሥራ ዘንድሮ ባለመከናወኑ ኃይቁ ላይ አደጋ መደቀኑን ነዋሪዎችና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ጣና ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች አረሙ ፈጥኖ እየተስፋፋ መሆኑን አመልክተዋል።

የአርሶ አደሮቹ ሥጋት በየቀኑ እየደረሰው መሆኑን የአማራ ክልል የጣና ኃይቅና ሌሎች ውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ገልፆ ወደ ቦታው ሄዶ ለመሥራት የክልሉ የፀጥታ ችግር እንቅፋት እንደሆነበት አስታውቋል።

SEE ALSO: እምቦጭ አረምን ከጣና ላይ የማስወገድ ዘመቻ

በምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ የሚሠሩት የአካባቢ ጥበቃና የሥነ ምኅዳር አያያዝ ባለሙያ አቶ መለሰ ተባባል የአረሙ የመሠራጨት ፍጥነት ለኃይቁ ህልውናም ሆነ በውስጡ ላሉ አካላት አደገኛ እንደሆነ አሳስበው የመቆጣጠርና የማስወገድ ሥራው በፍጥነት ካልተጀመረ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልፀዋል።

የክልሉ ባለሥልጣናት አንፃራዊ ሰላም መመለሱን ቢናገሩም እምቦጭን የማስወገድ እንቅስቃሴ ግን እንደቆመ መሆኑን በክልሉ በራሱ የተቋቋመው ኤጀንሲ አመልክቷል።

SEE ALSO: ጣና ሐይቅን የወረረው እምቦጭ ለማስወገድ ካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን

አረሙ በተለይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ ደንቢያ በኩል ባለው የኃይቁ ክፍል ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሠራጨ መሆኑን የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፋሲል ድልነሳ አስረድተዋል።

እምቦጭ የሚባለው መጤ አረም ጣና ላይ መታየት የጀመረው ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ ።

SEE ALSO: “ከተግባሩ በላይ ሐሳቡ የአንድነትን መንፈስ ያመጣል”- በእንቦጭ ዙሪያ የተሰባሰቡ ወጣቶች

የአረሙን ተፅዕኖ ለመከላከልና የሐይቁን ኅልውና ለመታደግ በተለይም ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ተፈጥሮ የመከላከልና የማፅዳት ዘመቻዎች በሃገር ውስጥም በዓለምአቀፍ ደረጃም ሲካሄዱ የነበረ ቢሆንም ኮቪድ 19፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ የክልሉ ፀጥታ መደፍረስ ሥራው እንዲቆም አድርገውታል።

አረሙ የጣና አዋሳኝ በሆኑ 3 ዞኖች፣ 9 ወረዳዎችና በ35 ቀበሌዎች 4ሺህ 300 ሄክታር ላይ ተስፋፍቶ ነበር።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡