የዊኪሊክሱ መሥራች ጁሊያን አሳንጅ ከሰዓታት በፊት ካንብራ፣ አውስትራሊያ ገብቷል። ትላንት ረቡዕ በሠላማዊ ውቅያኖስ የአሜሪካ ግዛት በሆነችው ሳይፓን የፌዴራል ፍ/ቤት ቀርቦ ከተከሰሰበት 18 የሚሆኑ ጉዳዮች ውስጥ በአንዱ ጥፋተኝነቱን አምኖ፣ ዳኛዋ በእስር ላይ የቆየበትን አምስት ዓመት ወደ ቅጣት ቀይረው ነፃ ያወጡት ጁሊያን አሳንጅ፣ በአውስትራሊያ መዲና ካንብራ የአየር ማረፊያ ደርሶ ከውሮፕላን እንደወረደ ባለቤቱን እና አባቱን አቅፎ ሲስም ተስተውሏል።
ባለፉት ወራት ውስጥ፣ በአሜሪካው የፍትህ መ/ቤትና በጁሊያን አሳንጅ ጠበቆች መካከል ድርድር ሲደረግ የቆየ ሲሆን፣ ጁሊያን አሳንጅ የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ መረጃዎችን አትሟል በሚል በቀረበበት ክስ በፍ/ቤት ቀርቦ ጥፋተኝነቱን የሚያምን ከሆነ፣ በእንግሊዝ ለአምስት ዓመታት የቆየበት የእስር ጊዜ ወደ ቅጣት ተቀይሮ ነጻ እንደሚወጣ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።
SEE ALSO: የዊኪሊክሱ ጁሊያን አሳንጅ ተላልፎ እንዳይሰጥ ሕጋዊ ጥረት በማደረግ ላይ ነውየአውስትራሊያ መንግሥት ከአስር ዓመታት በላይ የፈጀውን የሕግ ሂደት እንዲያበቃ ለአሜሪካ መንግስት ጥያቄ ማቅረቡ እና የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደርም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ፍላጎቱን መግለጹ፣ ትላንት በፍ/ቤት ለተደረሰበት የመጨረሻ ውሳኔ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተዘግቧል።
ጁሊያን አሳንጅ ከእ.አ.አ 2010 ጀምሮ በወቅቱ ብራድሊ ማኒንግ ተብሎ በሚጠራ በኋላ ግን ጾታውን ወደ ሴት ቀይሮ ቸልሲ ማኒንግ በሚል ከምትጠራ የቀድሞ የአሜሪካ መከላከያ ሠራተኛ ያገኛቸውን ጥብቅ የአሜሪካ መከላከያና ዲፕሎማሲያዊ ሰነዶችን በዊኪሊክስ ድህረ ገጹ ላይ በማተሙ ነበር ለመከሰስ የበቃው።
በተጨማሪም አሳንጅ የጾታ ጥቃት ፈጽሟል በሚል በስዊዲን ክስ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን፣ ከእንግሊዝ ተይዞ ወደ ስዊዲን እንዲተላለፍ የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ፣ በእ.አ.አ 2012 ለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቆ ለሰባት ዓመታት በኤምባሲው ጊቢ ውስጥ ኖሯል።
አሳንጅ ከኤምባሲውና ከኢኳዶር መንግስት ጋራ የነበረው ግንኙነት በመሻከሩም፣ ለእንግሊዝ መንግስት ተላልፎ ተሰጥቶ ላለፉት አምስት ዓመታት በከፍተኛ ጥበቃ ሥር በሚገኝ እስር ቤት ቆይቷል።
ትላንት በአሜሪካ ፍ/ቤት የተሰጠው ውሳኔ፣ ለ14 ዓመታት የቆየውን የጁሊያን አሳንጅ የተጓተተ ዓለም አቀፍ የሕግ ሂደት መቋጫ አበጅቶለታል።