በበርበራ ጉዳይ የሚመለከታቸው ወደ ዲፕሎማሲ እንዲገቡ ማሃማትና አሜሪካ መከሩ

Your browser doesn’t support HTML5

በበርበራ ጉዳይ የሚመለከታቸው ወደ ዲፕሎማሲ እንዲገቡ ማሃማትና አሜሪካ መከሩ

በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።

የበርበራ ወደብ ስምምነት ጉዳይ አፍሪካ ቀንድ ላይ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ለዲፕሎማሲ ንግግሮች እንዲቀመጡ የአፍሪካ ኅብረትና ዩናይትድ ስቴትስ አሳስበዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የምታውቀው የሶማሊያን የ1960 ዓ.ም. ወሰኖች ሉዓላዊነት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

የእሥላማዊ ትብብር ድርጅት ጠቅላይ ፅህፈት ቤት ከሶማሊያ ጎን እንደሚቆም ዛሬ አሳውቋል።

ሙሴ ቢሂ አብዲ ሃርጌሳ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ጠብቋቸዋል፤ ሞቃዲሾ ላይ ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አሜሪካን-ኢትዮጵያዊያን የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ የሚባል ቡድን የአውሮፓ ኅብረትን አቋም እንደሚደግፍ አስታውቋል።

ስምምነቱ ዩናይትድ ስቴትስን እንደሚያሳስባት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ትላንት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ “በስምምነቱ ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ ድንገት ያሻቀበው ውጥረት በሌሎች አጋሮች ላይ ያሳደረውን ብርቱ ሥጋት እንጋራለን” ብለዋል።

ሁሉም ወገኖች ወደ ዲፕሎማሲ ንግግር እንዲገቡ ያሳሰቡት ሚለር “ዩናይትድ ስቴትስ የምታውቀው የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ በአውሮፓ አቆጣጠር በ1960 ዓ.ም. ወሰኖቿ ውስጥ ላለ ሉዓላዊነቷና የግዛቷ ጥብቅነት ነው” ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ደግሞ፣ በኢትዮጵያ እና “የሶማሊያ ክልል” ባሏት ሶማሊላንድ መካከል የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረውን ውጥረት በቅርበት እየከታተሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

መልካም ግንኙነታቸውን ወደ ማበላሸት ሊወስድ ከሚችል ማንኛውም አድራጎት እንዲቆጠቡ”

ሊቀመንበሩ ትላንት ምሽት ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል እየተፈጠረ ያለውን ውጥረት ለማርገብ “መረጋጋት እና መከባበር እንዲኖር” ጥሪ አቅርበዋል። በዚህ ረገድ ሁለቱ ተጎራባች ሃገሮች ባለማወቅ “መልካም ግንኙነታቸውን ወደ ማበላሸት ሊወስድ ከሚችል ማንኛውም አድራጎት እንዲቆጠቡ” ሲሉም አሳስበዋል።

“ሶማሊያንና ኢትዮጵያን ጨምሮ የሁሉንም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገሮች አንድነት፣ የግዛት አሃድነት እና ምሉዕ ሉዓላዊነት ማክበር አስፈላጊ ነው” ያሉት ሊቀመንበር ሙሣ አክለውም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምን፣ ደኅንነትንና መረጋጋትን ለማስፈንና ለማጠናከር “የመልካም ጉርብትና ደንቦችን ማክበር ያስፈልጋል” ብለዋል።

ሁለቱ ወንድማማች ሃገሮች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት እጅግ ገንቢ በሆነ፣ በሰላማዊና በትብብር መንገድ ለመፍታት ያለምንም መዘግየት ድርድር እንዲጀምሩም አሳስበዋል። በዚህም ትብብራቸውን በማጠናከር ለቀጣናው ሰላምና ፀጥታ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል።

ለዚህ አዲስ የአፍሪካ ውጥረት አፍሪካዊ መፍትኄ ለመስጠት የአፍሪካ ኅብረት ከጎናቸው እንደሚቆምም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መሪዎች ሰኞ ታኅሳስ 22/2016 ዓ.ም. የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊላንድን “የግዛቴ አካል ነች” በምትላት ሶማሊያ ዘንድ ቁጣን መቀስቀሱ ይታወቃል።

ለኢትዮጵያ በሊዝ የባሕር በር፣ ለሶማሊላንድ ደግሞ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም በሂደት የነፃ ሃገርነት ዕውቅናን ከኢትዮጵያ እንድታገኝ ያስችላል የተባለው ይህ ስምምነት “ሉዓላዊነቴንና የግዛቴን አንድነት የሚጥስ ነው” ስትል ሶማሊያ አውግዛለች።

በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልም ሆነ ሃገር የለም” የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ “የተጣሰ ሕግም የተሰበረ እምነትም የለም”

“በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልም ሆነ ሃገር የለም” የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ “የተጣሰ ሕግም የተሰበረ እምነትም የለም” ሲል ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የሶማሊያ መንግሥት “ሉዓላዊነቴ እንዲቀጥል ከጎኔ ቁሙ” የሚል ጥሪ ለተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት ማቅረቡም ይታወሳል።

በእንግሊዝኛ መጠሪያው ምህፃረ ቃል “ኦአይሲ/OIC” በመባል የሚታወቀው የእሥላማዊ ትብብር ድርጅት ዋና ፅህፈት ቤት ዛሬ ጂዳ፣ ሳዑዲ አረቢያ ላይ ባወጣው መግለጫ “የሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሊከበር ይገባል” ብሏል።

57 አባል ሃገሮችን ያቀፈው ኦአይሲ በራሱ ቻርተርና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት “የአባል ሃገሮችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማክበር ያለውን ቁርጠኝነት” ጠቅሶ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ መነሻ በማድረግ “የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጥስ ማንኛውንም ድርጊት አልቀበልም” ሲል አስታውቋል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ደግሞ “ያለ ሶማሊያ መንግሥት እውቀት በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው ስምምነት አሳስቦናል” ብሏል።

“በዓለምአቀፍ ህግ እንደተደነገገው ሁሉ የቱርክ መንግሥት ለሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት ጥብቅነት ድጋፉን እንደሚቀጥል” አስታውቆ “በሶማሊያና በሶማሊላንድ መካከል ያሉ ውዝግቦች በሁለቱ ቀጥተኛ ንግግሮች እንዲፈቱ፣ ለዚህም የቱርክ መንግሥት ተንሳሽነቶችን እንደሚደግፍ በድጋሚ እንደሚያረጋግጥ” መግለጫው አስታውቋል።

SEE ALSO: ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር ውል ቋጠሩ

የአውሮፓ ኅብረትም “የሶማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሊከበር እንደሚገባ” ትናንት ገልፆ ነበር።

አሜሪካን-ኢትዮጵያዊያን የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ የሚባል ቡድንም የአውሮፓ ኅብረትን አቋም እንደሚደግፍ አስታውቋል።

ኮሚቴው በኤክስ ገፁ ላይ “በሃገሪቱ ሕገመንግሥት፣ በአፍሪካ ኅብረት ቻርተርና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሪያዎች መሠረት ለሶማልያ የግዛት አንድነት አስፈላጊነት አፅንዖት በመስጠት” ከአውሮፓ ኅብረት ጎን እንደሚቆም አመልክቷል። “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል እንደመሆኗ ዓለምአቀፍ ደረጃዎችን የመደገፍና የማክበር የሞራል ኃላፊነት አለባት” ብሏል።

ቡድኑ ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ መሆኗን አስታውሶ ሀገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች “ቀጣናዊ ግጭቶችን መቀስቀስ ግድ የለሽነት ነው” ሲል አክሏል።

ሞቃዲሾ ውስጥ ደግሞ ስምምነቱን የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች ዛሬም ቀጥለዋል።

ዛሬ የተሰበሰበው በጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዜ አብዲ ባሬ የተመራው የሶማልያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመግባቢያ ስምምነቱን በመቃወም “መንግሥታትና ዓለምአቀፍ ድርጅቶች አንፀባርቀዋል” ያለውን አቋም ማድነቁን፣ የሞቃዲሾው የቪኦኤ ዘጋቢ የላከው መረጃ ያመለክታል።

የሶማሊያ መንግሥት ቃል አቀባይ ፋርሃን መሀመድ ጂማሌ ስለ ካቢኔው ስብሰባ ሲያብራሩ “ካቢኔው በተለይ ታኅሣስ 22/2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ መንግሥትና በሶማሌ ሰሜናዊ ግዛት የሶማሌላንድ አስተዳደር መካከል በተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት የፈፀመውን ጥሰት ተመልክቷል” ብለዋል። አያይዘውም “የኢትዮጵያን እርምጃ በመቃወም የሶማሌ ህዝብ በአገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ያሳየውን ጀግንነት ካቢኔው አድንቋል፤ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሕዝብ ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የጀመረችውን ግልፅ ወረራ በመቃወም መንግሥታትና ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ያሳዩትን ጠንካራ አቋምና ውሳኔም አድንቋል’’ ብለዋል።

SEE ALSO: ኢትዮጵያ፣ ሶማሊላንድ፣ ሶማሊያ - የዛሬ ውሎ

በሌላ በኩል፣ ከአወዛጋቢው የመግባቢያ ስምምነት መፈረም በኋላ በኢትዮጵያ የቀናት ቆይታ ያደረጉት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ዛሬ ሃርጌሳ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሙሴ ቢሂ ሃገራቸው እንደተመለሱ ባደረጉት ንግግር የስምምነቱን ጭብጦች ያብራራ ንግግር አድርገዋል።

"የሶማሊላንድ ግዛት ሊሸጥ አይችልም። ማንም ፕሬዚዳንት መሸጥ አይችልም። በሁለተኛው የስምምነቱ አንቀፅ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተወሰነ ጊዜ መሬት በሊዝ እንዲሰጠው፣ መጠኑ ላይ እንዲወሰንና መሬትን በሊዝ መስጠትን በሚመለከቱ ዓለምአቀፍ ህጎች እንዲመራ የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መንግሥታት ተስማምተዋል። በምትኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሶማሊላንድ ዕውቅና የሚሰጥ ሲሆን ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያው እንደሚሆን በስምምነቱ ተካቷል” ብለዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ “በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል እየታዩ ያሉ ለውጦች እንደሚያሳስቧቸው” የገለፁት የምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት ባለሥልጣን ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ “እህትማማች” ያሏቸው ሁለቱ ሃገሮች ጉዳዩን “በሰላማዊ መንገድ ለመያዝ እንዲተባበሩ" ትላንት ባወጡት መግለጫ ጠይቀው ነበር።

የሶማሊያ መንግሥት በበኩሉ የኢጋድ ሥራ አስፈፃሚ ያወጡትን መግለጫ “ለኢትዮጵያ መንግሥት ያደላ ነው” በማለት በፅኑ እንደሚቃወመው አስታውቋል። የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ሥራ አስፈፃሚው በአስቸኳይ ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ መግለጫውን እንዲያነሱና ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን” ብሏል።

ከኬንያ ሰሜን ምሥራቅ ክልል የተወከሉ እንደራሴዎች ደግሞ የሰነዱን መፈረም ተከትሎ “እየታዩ ያሉ ፖለቲካዊ ለውጦች ያሳስቡናል” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል። ኢትዮጵያ “የሶማሊያን የግዛት አንድነት እንድታከብር”ም ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ምንም እንኳ ዓለምአቀፍ ዕውቅና ባይኖራትም ግንቦት 10/1984 ዓ.ም. ነፃ ሃገር መሆኗን ካወጀች አንስቶ ላለፉት 32 ዓመታት በራሷ እየተዳደረች ያለችው የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በሶማሌላንድ ሪፐብሊክና በኢትዮጵያ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ሊያከብሩ ይገባል” ሲል አሳስቧል።

“ሶማሊላንድ ለ32 ዓመታት ሉዓላዊነቷና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን አስከብራ ቆይታለች” ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ፣ አክሎም “ሶማሊላንድ ከብዙ ሃገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠርና በዓለምአቀፍ ትብብሮች በመሣተፍ የረጅም ጊዜ ዓለምአቀፍ ስምምነቶችን ፈፅማለች” ብሏል። የሶማሊላንድ መንግሥት ይህን ሲያደርግ በሶማሊላንድ ሕገመንግሥት መሆኑንና በግዛቱ ላይ ብቸኛ ሥልጣን እንዳለውም አረጋግጧል።

የሶማሊላንድ መንግሥት “ሉዓላዊ ሃገሮች ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት” ቀጣናዊ ትብብርን በሚያበረታቱ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ውስጥ መሣተፍ እንዳለባቸው በመግለፅ ሶማሊላንድ “ሉዓላዊ ሀገር” እንደሆነችም በአፅንዖት ተናግሯል።

ባለፉት ዓመታት ሶማሊላንድና ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የሰላምና የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ የወንድማማችነት ግንኙነት መሥርተዋል ሲል አስታውሷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደግሞ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ትናንት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ማብራሪያ መሰጠቱን በማኅበራዊ የመገናኛ ገፆቹ ያስታወቀው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዲፕሎማቶቹ ስለተነሱ ሃሣቦች ያነሳው ነገር የለም።

የአሜሪካ ድምፅ ስለጉዳዩ ከመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ያድምጡ፡፡