በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ፣ ሶማሊላንድ፣ ሶማሊያ - የዛሬ ውሎ


ኢትዮጵያ፣ ሶማሊላንድ፣ ሶማሊያ - የዛሬ ውሎ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:16 0:00

ኢትዮጵያ፣ ሶማሊላንድ፣ ሶማሊያ - የዛሬ ውሎ

በሶማሊላንድ ዕውቅና ጉዳይ አቋም እንደሚወስድ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።

ለኢትዮጵያ የባሕር በር፣ ለሶማሌላንድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ ያስገኛል የተባለውን ይህንን የመግባቢያ ሠነድ ሶማሊያ “በሉዓላዊነቷ ላይ የተቃጣ ጥቃት”፣ "ዋጋቢስና ህጋዊ መሠረት የሌለው ነው” ብላዋለች።

ኢትዮጵያ ደግሞ “በስምምነቱ የሚጎዳ ሀገርም ሆነ የተጣሰ ሕግ የለም” ብላለች።

ስምምነቱን የሚቃወም ግዙፍ ሰልፍ ሞቃዲሾ ላይ፣ ስምምነቱን የሚደግፍ ሌላ ግዙፍ የተባለ ሰልፍ ሃርጌሣ ላይ መካሄዳቸውን ሪፖርተሮቻችን ዘግበዋል።

የሶማሊላንድ ፓርላማ ዛሬ ተሰብስቦ ለዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ መልዕክት አስተላልፏል።

ለኢትዮጵያ በአደን ባሕረሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር ኃይል መደብና የባሕር ላይ ንግድ አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል የሚያስገኝ ነው”

የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ (ረቡዕ) ባወጣው መግለጫ ሰነዱ “ለኢትዮጵያ በአደን ባሕረሰላጤ ላይ ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር ኃይል መደብና የባሕር ላይ ንግድ አገልግሎት በሊዝ የምታገኝበትን ዕድል የሚያስገኝ ነው” ብሏል።

“ሶማሊላንድ ደግሞ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲኖራት ያስችላል” ሲልም መግለጫው አክሏል።

ስምምነቱ ለኢትዮጵያና ለሶማሊላንድ መሪዎች የእርካታ፣ ሶማሊያ ውስጥ ደግሞ የቁጣ ሰበብ መሆኑ እየታየ ነው።

ሰነዱ “በሂደት ሶማሊላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበትን አግባብም ያካትታል” ብሏል የኢትዮጵያ መንግሥት።

በሌላ በኩል የመግባቢያ ሰነዱን "ዋጋ ቢስ እና ህጋዊ መሠረት የሌለው ነው” በማለት የተቃወመው የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ እርምጃ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጥስ “ግልፅ ጥቃት ነው” ሲል አውግዟል።

“በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልም ሆነ ሀገር የለም” የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ “የተጣሰ ሕግና የተሰበረ እምነትም የለም” ሲልም በኮምዩኒኬሽን አገልግሎቱ መግለጫ ጠቅሷል። ሆኖም “በዚህ አወንታዊ ድምዳሜ የሚከፋ፣ የሚደነግጥና ሁኔታውን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል አይኖርም አይባልም” ሲል አክሏል።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼኽ መሀሙድ ትላንት ለፓርላማቸው ባደረጉት ንግግር “የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነትና ዓለምአቀፍ ህግን የሚፃረር ነው” ሲሉ አውግዘውታል።

ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ኢትዮጵያ ብቸኛ ሃገር እንዳልሆነች የገለፀው የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ሶማሊላንድ የተሟላ ዕውቅና ባታገኝም የዛሬ 32 ዓመት ነፃነቷን ካወጀች ወዲህ “የወደብ አገልግሎትና ልማትን ጨምሮ ከአንዳንድ ሃገሮች ጋር ስምምነት መፈረሟን” በማሳያነት አንስቷል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ ሃገሮች ሐርጌሳ ውስጥ ቆንስላ ከፍተው እንደሚንቀሳቀሱም ያነሳው የመንግሥቱ መግለጫ ከዚህ ቀደም በርበራ ላይ ኢትዮጵያ የ19 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት ይፈቅድ የነበረ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ እንደነበርም አስታውሷል።

በአሁኑ ወቅት “ሌሎች ሃገሮችም ተመሳሳይ ሂደት እየተከተሉ ነው” ያለው መግለጫ ኢትዮጵያ አሁን የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድና ሂደትም “በመሠረቱ አንድና ያው ነው” ሲልም አክሏል።

ኢትዮጵያ በ2006 ዓ.ም. “እሥላማዊ ችሎቶች ይባሉ የነበሩ ሞቃዲሾን ይዘው የነበሩ ኃይሎችን ለመውጋት ወደ ሶማሊያ መግባቷ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ሥጋት የሆነው ፅንፈኛ ቡድን አልሸባብ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል” ያሉት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ከዚህ በኋላም የኢትዮጵያ መገኘት “ለአክራሪነት መስፋፋት መንስዔ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

አል ሸባብም “የሶማሊያ ህዝብ መሬቱንና ባህሩን ከውጭ ሥጋት ለመከላከል እንዲተባበር በቃል አቀባዩ በኩል አሳስቧል” ሲል አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ደግሞ “ስምምነቱ ለአፍሪካ ቀንድ ትስስር የላቀ ፋይዳ ያለው ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት የሚገባትን ሚና እንድትጫወት የተሻለ ዕድል ይፈጥራል” ብሏል።

ይህ በንዲህ እንዳለ የሶማሊያ መንግሥት የጠራውና ቁጥሩ እጅግ ግዙፍ እንደሆነ የተነገረለት ስምምነቱን የተቃወመ ሰልፍ ሞቃዲሾ የእግር ኳስ ስታዲየም ውስጥ ተካሂዷል። በተመሣሳይ ሁኔታም በግብታዊነት የተሰባሰበ ነው የተባለ ሌላ አነስተኛ የተቃውሞ ሰልፍም ሶማሊላንዷ ሃርጌሳ ውስጥ ተደርጓል። በሞቃዲሾው ሰልፍ ላይ የተናገሩት የአገርግዛት ሚኒስትር አህመድ ሞዓሊም ፊቂ “የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እርምጃ አይቀበልም” ብለዋል። ቪኦኤ ካነጋገራቸው ሰልፈኞች አንዱ “ሶማሊላንድ የሶማሊያን መሬት መስጠት አትችልም፤ ቢሂ ያደረጉት ስህተት ነው” ብሏል።

በሌላ በኩል ግን የሶማሊላንድ መንግሥት የጠራውና ግዙፍ ነው የተባለ ስምምነቱን የሚደግፍ ሰልፍ ሃርጌሳ ውስጥ ሃይሬአ አደባባይ ላይ እየተካሄደ መሆኑን እዚያው የሚገኘው ዘጋቢያችን ማምሻውን ገልፆልናል። ሞቃዲሾ ላይ ያለው የቁጣ ስሜት ሲሆን ሃርጌሳ ከተማ ውስጥ ግን ነዋሪው በየመንገዱ ደስታውን እየገለፀ መሆኑን ሪፖርተራችን አመልክቷል።

በሞቃዲሾው ሰልፍ ላይ ስምምነቱን የሚቃወሙት የሶማሊያ፣ በሃርጌሳው ላይ ደግሞ የሚደግፉት የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ሶማሊላንድ ነፃ ሃገር ነች፤ የራሷን የብስ፣ ባህርና ዓየርም የምትቆጣጠረው ራሷ ነች”

የሶማሊላንድ ካቢኔ ዛሬ ተሰብስቦ ለዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ባስተላለፈው መልዕክት “ሶማሊላንድ ነፃ ሃገር ነች፤ የራሷን የብስ፣ ባህርና ዓየርም የምትቆጣጠረው ራሷ ነች” ማለቱን የሶማሊላንድ የማስታወቂያ ሚኒስትር አሊ ሃሰን ሞሃመድ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

ለአሜሪካ ድምፅ ትናንት ሃሣባቸውን ያካፈሉት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የዓለምአቀፍ ጉዳዮች መምህር ዶ/ር አብዱ መሃመድ አሊ ስምምነቱ ሊኖረው ይችላል ያሉትን መዘዝ ጠቁመው ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃት ተናግረዋል።

የፖለቲካና የዓለምአቀፍ ግንኙነቶች ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር በፍቃዱ ዳባም ይህንኑ ሀሳብ አጠናክረዋል።

ናይሮቢ የሚገኘው "የሳሃን ምርምር ተቋም” የሥልታዊ ጉዳዮች አማካሪ ማት ብራይደን “ስምምነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀጣናው መረጋጋት ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም” ማለታቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

“ሶማሊያ ፍላጎቷን በሶማሊላንድ ላይ በኃይል ልትጭን የምትችልበት መንገድ የላትም” ያሉት ብራይደን “እንድትገለል ለማድረግ ግን ሕጋዊ የሉዓላዊነት መሣሪያዎችን ልትጠቀም እንደምትችል” ጠቁመዋል። ከእነዚህም መካከል የእርዳታ ድርጅቶችንና የለጋሽ መንግሥታትን እንቅስቃሴ መገደብ፣ ዓለምአቀፍ በረራዎችን መከልከልና የውጭ ንግድ አንቀሳቃሾች ከሶማሊላንድ ጋር እንዳይሠሩ ማስጠንቀቅ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

ሆኖም በረዥም ጊዜ እንደ ጂቡቲና ኤርትራ ካሉ ጎረቤት ሃገሮች ጋር የፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶች መባባሳቸው “አይቀርም” ብለዋል ብራይደን።

በሌላ በኩል የመግባቢያ ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ “በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል እየታዩ ያሉ ለውጦች እንደሚያሳስቧቸው” የምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት ባለሥልጣን ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ዛሬ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ሥራ አስፈፃሚው “እህትማማች” ያሏቸው ሁለቱ ሀገሮች ጉዳዩን “በሰላማዊ መንገድ ለመያዝ እንዲተባበሩ" ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት “የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ አንድነትን፣ ሉዓላዊነትንና የግዛት አሃድነትን ማክበር አስፈላጊ ነው” ብሏል። ይህ “ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ነው” ሲሉ የኅብረቱ ቃል አቀባይ ትናንት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የትላንቱን ስምምነት በተመለከተ አስተያየታቸውን ከሰጡ ግለሰቦች መካከል የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናዥ ስምምነቱን “ድንቅ ዜና” ሲሉ አሞካሽተውታል።

አምባሳደር ናዥ በኤክስ ገፃቸው ላይ ባሠፈሩት ፅሁፍ “ሶማሊላንድ የባህር ዳርቻን ለኢትዮጵያ የማከራየት ስምምነቷ ሲጠናቀቅ ዕውቅና ሊሰጣት ይገባል” ብለዋል። “እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲሉም ስሜታቸውን አጋርተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG