የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ገቡ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ ሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ

ሁለቱ ሃገሮች ካይሮ ላይ ወታደራዊ ስምምነት በተፈራረሙ ሁለት ሳምንታት እድሜ ሁለት የግብፅ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ዛሬ ማክሰኞ ሞቃዲሾ ገብተዋል።

ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ እና ወታደራዊ መኮንኖችን ያሳፈሩት ሁለት ሲ-130 ወታደራዊ አውሮፕላኖች ከሞቃዲሾው አደን አዴ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሳቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሁለት የሶማሊያ ምንጮች አመልክተዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ መሀሙድ ባለፈው የነሃሴ ወር ካይሮ በጎበኙበት ወቅት ሞቃዲሾ እና ካይሮ የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት፤ ‘የሁለቱን አገሮች ትብብር ያጎለብታል’ ብለው እንደሚያምኑ የሶማሊያ ባለስልጣናት ይናገራሉ።

ይህንን አስመልክቶ ሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አህመድ ሙአሊም ፊቂ በሰጡት አስተያየት "ሶማሊያ እና ግብፅ ካይሮ ላይ የተፈራረሙት ይህ ወታደራዊ ስምምነት ወሳኝ በሆነ ጊዜ ላይ የተፈጸመ፤ ሽብርተኝነት ለመዋጋት የምናደርገውን ጥረት የሚያግዝ እና ሉዓላዊነታችንን በብቃት ለማስከበርም የመከላከያ ሰራዊታችን አቅም የሚያጎለብት ነው" ብለዋል።

በሌላ በኩል እርምጃው እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በ2024 መጀመሪያ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን አወዛጋቢ የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት እያሽቆለቆለ ባለበት ወቅት የተወሰደ መሆኑም ተመልክቷል።

SEE ALSO: ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር ውል ቋጠሩ

በሌላ ተያያዥ ዜና ሞቃዲሾ በአሁኑ ወቅት በዚያች አገር የተሰማራውን የአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ተልዕኮ በመጪው የአውሮፓውያኑ ጥር 2025 በሚተካው የአፍሪካ ሕብረት-መር የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ግብጽ እንድትሳተፍ የምትሻ መሆኗን አስታውቃለች።