በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ግብፅ በሶማሊያ እና በደህንነቷ ላይ የሚደቀን ስጋት እንዲኖር አትፈቅድም - ፕሬዝዳንት ሲሲ


በርበራ፣ ሶማሌላንድ
በርበራ፣ ሶማሌላንድ

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ለሶማሌላንድ ነፃነት እውቅና መስጠቱን እንደምታስብበት ማስታወቋን ተከትሎ፣ የግብፅ ፕሬዝዳንት በሶማሊያ ላይ ምንም አይነት ስጋት እንዲኖር እንደማይፈቅዱ እሁድ እለት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ የሰጡት አስተያየት፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሻከረ ግንኙነት ያላት ግብፅ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ከሰጠችው አስተያየት እጅግ በጣም ጠንካራው ሲሆን፣ ግብፅ፣ በርካታ አለመረጋጋቶች ባሉበት የአፍሪካ ቀንድ በተፈጠረው አዲስ ውጥረት ውስጥ እጇን ልታስገባ እንደምትችል ያሳየ ነው ተብሏል።

ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሲሲ "ግብፅ ማንም ሶማሊያን እንዲያስፈራራም ሆነ ደህንነቷን አደጋ ላይ እንዲጥል አንፈቅድም" ብለዋል።

ሲሲ አክለው "ግብፅን አትፈታተኑ፣ ወይም ወንድሞቿን አታስፈራሩ፣ በተለይ ደግሞ ጣልቃ እንድንገባ ከጠየቁ" ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ አመልክቷል።

ወደ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የፈፀመችው ስምምነት፣ ኢትዮጵያ 20 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የባህር ጠረፍ ለ50 አመታት እንድትከራይ እና ለንግድ እና የጦር ሰፈር አገልግሎት እንድትጠቀም የሚፈቅድ ነው። በምትኩ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድን የነጻ ሀገር ዕውቅና ልትሰጣት እንደምትችል አስታውቃለች። ሶማሌላንድን የሀገሯ አካል አርጋ የምትቆጥረው ሶማሊያ ግን ይህንን ስምነት ተቃውማለች።

"ለኢትዮጵያ የማስተላልፈው መልዕክት፣ መሬትን ለመቆጣጠርና ለመያዝ መመኮር ማንም የማይስማማበት ጉዳይ ነው" ያሉት አል-ሲሲ የተሻለው መንገድ በልማት ላይ መተባበር ነበር ብለዋል።

በግብፁ መሪ ንግግር ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ ሮይተርስ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ቢጠይቅም፣ ወዲያው ምላሽ አልሰጡም።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት፣ ኢትዮጵያ ለቀጠናው የአለመረጋጋት ምንጭ ሆናለች ሲሉ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ ግን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስተያየቱ "የማይረባ" ነው ሲል ምላሽ ሰጥቶ ነበር።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG