ኤም-ፔሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀመረ

የአውቶቡስ ጣቢያ በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የኬኒያው ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት አገልግሎት ጀመረ።

ከአፍሪካ ግዙፍ ምጣኔኃብቶች አንዷ እንደሆነች በሚነገርላት ኢትዮጵያ አገልግሎቱን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ ያለው የኬንያው የቴሌኮምዩኒኬሽን ኩባኒያ ሳፋሪኮም ኤም-ፔሳ የሚባለውን በሞባይል ስልክ የሚፈፀም የገንዘብ ልውውጥ አገልግሎት ትናንት ረቡዕ ጀምሯል።

በከፊል የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮምና የብሪታኒያው ቮዳፎን ኩባኒያዎች ንብረት የሆነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ዓመት የስልክና የዳታ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ ከ2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን አፍርቷል።

“ኤም-ፔሳ” የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ የገለፁት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ተጠባባቂ ሥራ አስፈፃሚ ስታንሊ ጆሮጌ “ደንበኞቻችን ከዚህ አገልግሎት የሚያገኙትን ጥቅም ለማሳደግ መሥራታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ኬንያ ውስጥ የ“ኤም-ፔሳ” አገልግሎቱን የዛሬ አሥራ ስድስት ዓመት (እአአ በ2007 ዓ.ም.) የጀመረው ሳፋሪኮም ከፍተኛ ትርፍ እያስመዘገበ መሆኑንና ግብፅ፣ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሌሶቶ፣ ሞዛምቢክና ታንዛኒያ ውስጥም እንደሚሠራ ታውቋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ይዞታነት የቆየውን የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት መንግሥቱ የዛሬ አራት ዓመት ለግሉ ዘርፍ መክፈቱን ተከትሎ የገባ የመጀመሪያው የውጭ የግል የቴሌኮም ኩባኒያ ነው።

ከመቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ የህዝብ ቁጥር ባላትና “ወጣት” በሚባል የዕድሜ ክልል ውስጥ ባለ ሰዋ ብዛት ደግሞ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናቸው ከሚባሉ ሃገሮች ተራ በምትገኘው ኢትዮጵያ በመጭዎቹ ዓመታት ግዙፍ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ኩባንያው እምነቱን እየገለፀ ነው።

አገልግሎቱ ግዙፍ ለሆኑ ዕድሎች በር እንደሚከፍት የሚናገሩ ተንታኞች ፈጣን ውጤት ለማስመዝገብ ሳፋሪኮም ግዙፍ መዋዕለነዋይ መመደብ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራውን ለመጀመር ከፍተኛ ነዋይ እንዳፈሰሰ ይህም ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረበት የሚነገለት ሳፋሪኮም ካለፈው ታኅሳስ 22 እስከ መጋቢት 22 በነበሩት ሦስት ወራት ውስጥ የነበረው ገቢ በአንድ አምስተኛ ቀንሶ እንደነበር የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

ከዚያ ወዲህ ባለው የሃገሪቱ የፋይናንስ ዓመት ውስጥም ትርፉን ከእጥፍ በላይ ካሳደገው ከኢትዮ ቴሌኮም ብርቱ ፉክክር እንደተደቀነበት ይነገራል።

ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌብር” በሚባለው የሞባይል ስልክ የገንዘብ ልውውጥ አገልግሎቱ ከ34 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማግኘቱን ባለፈው ወር አስታውቋል።