መሠረቱን በኬንያ ያደረገው ሳፋሪኮም፣ ዊም ቫንሄለፑትን ከመጭው መስከረም ጀምሮ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ መሾሙን አስታውቋል፡፡
የኩባንያውን የውስጥ ማስታወሻ ትናንት ማክሰኞ ማግኘቱን ጠቅሶ የዘገበው ሮይተርስ፣ ቫንሄለፑት ድርጅቱን ላላፉት ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል ብሏል፡፡
የቤልጅየም ዜጋ የሆኑት አዲሱ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ፣ በኢትዮጵያ ትልቅ የገበያ ትልሞችን ይዞ ባለፈው ዓመት ሥራ የጀመረውን ድርጅት የዕድገት ውጥኖች የማሳካት ኃላፊነት እንደሚኖራቸው ተነግሯል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ቴሌኮም ኩባንያ የሆነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ፣ አዲስ ደንበኞች ከማፍራት ውጭ፣ ባለፈው ግንቦት የሞባይል የገንዘብ ክፍያ አገልግሎት የመስጠት ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ አግኝቷል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ከመጭው መስከረም ጀምሮ ኤም ፔሳ የተሰኘውን አዲስ የገንዘብ ክፍያ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተመልክቷል፡፡