በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከሥራ ማስጀመሪያ ወጪው ጋራ በተያያዘ ገቢው ቀነሰ


ሳፋሪኮም ሱቅ ናይሮቢ፣ ኬንያ
ሳፋሪኮም ሱቅ ናይሮቢ፣ ኬንያ

የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመጀመር ባወጣው ወጪ የተነሣ፣ በዚኽ ዓመት እስከ መጋቢት ወር የነበረው ገቢ፣ በአምስት እጅ መቀነሱን፣ ድርጅቱ፣ ዛሬ ኀሙስ በሰጠው መግለጫ አመለከተ፡፡

ከፊል ንብረትነቱ፣ የደቡብ አፍሪኮው ቮዳኮም እና የእንግሊዝ ቮዳፎን የኾነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ ሥራውን የጀመረው፣ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት መገባዳጃ ላይ ነበር፡፡ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላት ኢትዮጵያ ያለውን የአገልግሎት መጠን፣ ከአምስት ዓመት ኢንቨስትመንት በኋላ በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ መነሣቱን፣ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ፣ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ቋሚ ደንበኞች እንዳሉት፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፒተር ንዴግዋ፣ ለኢንቨስተሮች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቱ፣ 150 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል፣ የሞባይል የገንዘብ ክፍያ አገልግሎት የመስጠት ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ማግኘቱን፣ ሥራ አስፈጻሚው መግለጻቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡

“በኢትዮጵያ ያለው ዕድል፣ ዝቅተኛ ግምት ሊሰጠው አይችልም፤” ያሉት ሓላፊው፣ በሚቀጥለው ሩብ ዓመት አጋማሽ ላይ፣ ድርጅቱ፣ የሞባይል የገንዘብ ክፍያ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

የሳፋሪኮም ገቢ፣ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ፣ ከወለድ እና ከታክስ በፊት 84ነጥብ 99 ቢሊዮን ሽልንግ ወይም 622ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር እንደኾነ፣ በሮይተርስ ዘገባ የተገለጸ ሲኾን፣ ካለፈው ዓመት ጋራ ሲነጻጸር፣ በ22 ከመቶ መቀነሱ ተመልክቷል፡፡

የኩባንያው የአክስዮን ዋጋ፣ ሦስት በመቶ በመቀነስ፣ ወደ 14ነጥብ 80 ሽልንግ መውረዱም ታውቋል፡፡

XS
SM
MD
LG