በሱዳን የተከሰተው ረሃብ ከቸነፈር ደረጃ ላይ መድረስ ያለመድረሱን ለመወሰን የመንግሥታቱ ድርጅቶች የተለያዩ ተቋማት እና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ባቀረቡት የቅድመ ትንበያ ውጤት መሰረት፣ ከ756 ሺሕ ሕዝብ በላይ ለከፋ የምግብ እጥረት ሊጋለጥ እንደሚችል ተሰግቷል።
የመጀመሪያው የትንበያ አሃዞች፤ እስካለፈው ግንቦት 24, 2016 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ በጦርነት በተበታተነችው አገር ውስጥ የታየውን 'በፍጥነት እያሽቆለቆለ ያለ ሁኔታ የሚያመላክቱ ናቸው’ ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በሰጡት አስተያት፣ በዓለም ግዙፍ የሰብአዊ ቀውስ በተከሰተበት የሱዳን ምስቅልቅል 12 ሚሊዮን ሕዝብ ከቀዬው መፈናቀሉን ተናግረዋል።
"በአንዳንድ ግዛቶች እጅግ መጠነ ሠፊ የረሃብ አደጋ በተንሰራፋበት ባሁኑ ወቅት ነዋሪዎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እና መድሃኒቶችን የማያገኙ በመሆናቸው ለሕልፈት እየተዳረጉ ነው" ሲሉ አክለዋል።
በተቀናጀ የምግብ ዋስትና የደረጃ ምደባ አሰራር መሰረት በሰኔ እና በመስከረም ወር መሃከል ባለው ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው 756, 000 የሚጠጉ ሰዎች የከፋ ውድመት ሊያስከትል በሚችለው ደረጃ 5 ውስጥ እንደሚገቡ የቅርብ ጊዜያቱ ትንበያዎች ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳኑ ብሔራዊ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ባለፈው ዓመት የሚያዝያ ወር የተቀሰቀሰው ውጊያ አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል።