ለሮበርት ሙጋቤ ውድቀት አንዱ ምክንያት እጅግ ለተራዘመ ጊዜ ሥልጣን የሙጥኝ ብለው መቆየታቸው መሆኑንና ቀደም ብለው አስረክበው ቢሆን ኖሮ እንደጀግና እንደተወደሱ ይኖሩ እንደነበር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ለቪኦኤ በሰጡት ትንታኔ አብራርተዋል።
ሥልጣኑ ላይ ያለው ዛኑ-ፒኤፍ በመሆኑ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚደርስባቸው ችግር አይኖርም ብለው እንደሚያስቡም ተናግረዋል ሻለቃ ዳዊት።
በደርግ ዘመን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በኋላም የኤርትራ አስተዳዳሪ የነበሩትና ከደቡባዊ አፍሪካ ሃገሮች የነፃነት ትግሎችና የኢትዮጵያ ሚና ጋር ተያይዞ አስፈፃሚ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ አሁን የሚሠሩት እራሣቸው ባቋቋሙት በአፍሪካ ሥልታዊና የደኅንነት (የፀጥታ) ጥናቶች ኢንስቲትዩት ተብሎ በሚጠራ ድርጅት ውስጥ ነው።
ኢንስቲትዩቱ ከምርምር ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከተለያዩ ድርጅቶችና ሃገሮች ጋር እየተባበረ አፍሪካ ውስጥ በሚታዩ ሕገወጥ የሰዎች ትልልፍ፣ በሰዎች የአካል ክፍሎች መነገድ፣ እንዲሁም የአደንዛዥ ዕፅዋትና ቅመማ ቅመምና የጦር መሣሪያዎች ዝውውር፣ የድህነት ደረጃና ሌሎችም 'የአፍሪካ መከራዎች ናቸው' በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን እየሠራ እንደሚያወጣ ሻለቃ ዳዊት ገልፀዋል።
በአፍሪካ፣ በተለይ ደግሞ በደቡባዊ አፍሪካ የነፃነት ትግሎች ውስጥ ኢትዮጵያ ተጫውታለች የሚባለው ሚና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ሆነ በደርግ ዓመታት ግዙፍ ነው። ለሽምቅ ተዋጊዎች የጦር ሥልጠና መስጠት፣ እንደነ ሮበርት ሙጋቤ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ጃሽዋ ንኮሞ፣ ኦሊቨር ታምቦን ከመሳሰሉ መሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነቶችን ማድረግን ያካተቱ ነበሩ ግንኙነቶቹ።
ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ እንዲህ ዓይነት ቁልፍ ኃላፊነት ይዘው የሚያስፈፅሙ ሰው ነበሩ።
ስለሰሞኑ የዚምባብዌ ሁኔታ ከቪኦኤ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ አንተርሶ የተቀናበረውን ዘገባና ሙሉውን ቃለ ምልልስ ከተያያዙት የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ