በሀረር ተወልዳና አድጋ የምህንድስና ትምህርት ለመከታተል መቀሌ ዩንቨርስቲ የሄደችው ሄርሜላ በ2001 ዓ.ም የሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያለች ያላሰበችው አጋጣሚ ተፈጠረ። እውቁ የሆሊውድ ፊልም ተዋናይ ማት ዴመን በትግራይ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ እርዳታ ለማድረግ ሲመጣ በሥራዎቹ የምታደንቀውንና የምታከብረውን ተዋናይ በአካል ለማየት እድል ገጠማት።
“አጋጣሚው ፣ በተለይ በገጠራማው የትግራይ ክልል ያለውን የውሃ አቅርቦት ችግርና በዛ ምክንያት የሚደርሰውን እንግልት ለመጀመሪያ ጊዜ እኔና ጓደኞቼ እንድናስተውል ረዳን ትላለች” ሄርሜላ።
ሄርሜላና ሌሎች ስድስት የትምህርት ቤት ሴት ጓደኞቿ “ለጠበታ ውሃ እንርዳ” የሚል ክለብ መስርተው ባሰባሰቡት ገንዘብና ማት ዴመንን አስመጥቶት በነበረው የማኅበር ረድኤት ትግራይ አጋዥነት የመጀመሪያውን የውሃ ጉድጓድ እንደርታ ወረዳ ላይ አስቆፍረው አስመረቁ። በውቅቱ የ 21 ዓመት ወጣት የነበረችው ሄርሜላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችውን የኅብረተሰቡን የውሃ ችግር ስታይ የተሰማትን “በቃላት ለመግለፅ ይከብዳል” ትላለች።
ርሜላ የምህንድስና ትምህርቷን አጠናቃ ከተመረቀች በኃላ በኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ሥራ ጀምራ ነበር። ነገር ግን በእንደርታ ያየችውን የውሀ እጦት ችግር ልትረሳው ባለመቻሏ ከወራት ያልዘለለ ዕድሜ የሠራችበትን መስሪያ ቤት ለቃ 'ጠብታ ውሃ' ሀገር በቀል ምግባረ ሰናይ ድርጅትን መሰረተች። ድርጅቱ በዐስር ዓመት ጉዞው በአምስት ክልሎች ላይ 70 የውሀ ጉድጓዶችን አስቆፍሮ 24 ሺህ ኢትዮጵያውያንን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ አድርጏል።
ኤልፋዝ ካሳ በጠብታ ውሃ ድርጅት ውስጥ የፕሮግራም ዳይሬክተር ነው። ሄርሜላና ጉዋደኞቿ የውሃ ክለቡን በዩንቨርስቲው ሲመሰርቱ በጎ ፍቃደኛ ሆኖ ያገለገለውና የቅርስ ጥበቃ ትምህርቱን ጨርሶ ሲመረቅ በቀጥታ ከሄርሜላ ጋር መሥራት የጀመረው ኤልፋዝ የሄርሜላ ሥራ የብዙ ቤተሰቦችን ህይወት የቀየረ ነው ይላል።
ሰው ያለውሃ መኖር አይችልም የሚለው ኤልፋዝ ከሄርሜላ ጋር በጠብታ ውሃ የሚሠሩት ሥራ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያመጣውን ለውጥ ያስረዳል።
“ውሃ ሰብዓዊ መብት ነው፣ ውሃ ማጣት የሴቶችና የህፃናትን የመማር፣ የመስራትና እራሳቸውን የመቻል መብታቸውን ይጋፋል” የምትለው ሄርሜላ በጎ ሥራን የተማረችው በሕክምና ሞያ ከተሰማሩት እናቷና ቤተሰቦቿ መሆኑን ትገልፃለች። “በተለያዩ የኢትዮጵያ ገጠር ክፍሎች የሚኖሩ ኅብረተሰቦችም የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግራቸው ሲቀረፍላቸው የሚታያቸው ትልቅ ደስታና ተስፋ ለስራዬ ጉልበት ነው” ትላለች።
ሄርሜላ አያይዛም
“የንፁህ ውሃ አቅርቦት በጤና ላይ ይደርሱ የነበሩ ችግሮችን ከማቃለሉ በላይ በተለይ ህፃናት በውሃ ፍለጋ ይጠፋ የነበረ ጊዜያቸውን በትምህርት እንዲያሳልፉ፣ መምሕራንም ያለችግር በማስተማር ሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ ረድቷል።”
ብላለች።
ከውሃ ማስቆፈር ሌላ 'ጠብታ ውሃ ድርጅት' የተቆፈሩት ጉድጓዶች በዘላቂነት ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገዶች ላይ እና ትምህርት፣ የንፅህና አጠባበቅ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ አመጋገብ ላይ የተለያዩ ስራዎች ይሠራል። ሄርሜላም በቀጣይ ድርጅቱ አድጎ በሥራው ተደራሽ ያላደረጋቸው ክልሎች ላይም የውሃ ችግሮችን የመቅረፍ እቅድ እንዳላት ትገልፃለች።
(የተያያዘውን የድምፅ ፋይል በመጫን ዘገባውን በድምፅ ማዳመጥ ትችላላችሁ)