ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረ ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ ዘጠኝ መቶ ሃምሣ ሰው ለኮሮናቫይረስ መጋለጡ መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር ባወጣው የክትትል ሪፖርት አስታውቋል።
ዝርዝሩ እንደሚያሳየው ከፍተኛው ቁጥር በተመዘገበባት አዲስ አበባ 324 ሰው፣ በኦሮምያ 249፣ በትግራይ 101 ተጋልጧል።
ከመቶ ያነሰም ቢሆን ከፍተኛ ቁጥሮች በደቡብ፣ በአማራ፣ በሲዳማ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በሃረሪ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በሶማሌ ክልሎችና ድሬ ዳዋ ውስጥ ተመዝግበዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ 35 ሺህ 791 ሰው ኮቪድ 19 ህመም ላይ እንደሚገኝና 21 ሺህ 102 ሰው ከህመሙ ማገገሙ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ያለፉ 17 ህይወቶችን ጨምሮ እስካሁን 897 ሰው በኮቪድ 19 ምክንያት መሞቱን የጤና ሚኒስቴሩ የዛሬ ሪፖርት አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ህንድ ውስጥ ቁጥሩ ወደ 86 ሺህ 500 የሚጠጋ ሰው ዛሬ ብቻ ለኮሮናቫይረስ መጋለጡ ተዘግቧል። በዚህም መሠረት የህንድ የኮቪድ 19 ተጋላጭ ቁጥር ከአራት ሚሊየን በላይ መሆኑን የጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮናቫይረስ መረጃ ማዕከል አስታውቋል።
አሁን ባለው ሁኔታ ከህንድ የበለጠ የኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ቁጥር ያላቸው ዩናይትድ ስቴትስና ብራዚል ሲሆኑ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 6 ሚሊየን 2 መቶ ሺህ ሰው ኮሮናቫይረስ ተላልፎበታል።
ሜክሲኮ ውስጥ ኮቪድ 19 እያደረሰ ባለው የከፋ ጥፋትና ሞት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ቫይታል ስታቲስቲክስ መዝጋቢ ቢሮዎች የሞት ማረጋገጫ የምሥክር ወረቀት መጨረሳቸው ተነግሯል።
በኮቪድ 19 ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 187 ሺህ 768 ሰው፣ ብራዚል ውስጥ 125 ሺህ 502 ሰው ህንድ ውስጥ 69 ሺህ 561 ሰው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት መሞቱን ጃንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።
በዓለም ዙሪያ በኮቪድ 19 ሰባት ሺህ የሚሆኑ የጤና ሠራተኞችና ባለሙያዎች መሞታቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚሆን ደኅንነቱ የተረጋገጠና ውጤታማ ክትባት በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል እስከመጭው የአውሮፓ ዓመት አጋማሽ ላይደርስ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።
ከድርጅቱ ዋና መቀመጫ ጄኔቫ የተጠናቀረው ዘገባ ዝርዝሩን ይዟል።
ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡት።