በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መንግሥት ትዕግሥቱ ተሟጥጧል - የትግራይ የፀጥታ ኃላፊ


ፋይል ፎቶ - የትግራይ ክልል እ.አ. አ. 2004
ፋይል ፎቶ - የትግራይ ክልል እ.አ. አ. 2004

ፖሊስ እየጠራ እንደሚያስፈራራቸው የወልቃይት - ማይ ካድራ ሰዎች ተናገሩ።

በወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ላይ ውሣኔ እንዲሰጠን ለፌደራል መንግሥት ባስገባነው ጥያቄ ምክንያት ዛቻና ወከባ እየደረሰብን ነው ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ስሞታ እያሰሙ ነው።

በምዕራባዊ ትግራይ ዞባ በቃስታ ሁመራ ወረዳ ውስጥ በምትገኘውና ከሱዳን ጋር በምትዋሰነው ማይ ካድራ ቀበሌ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ፖሊስ ሰዉን እየጠራ እያስፈራራ ወረቀት ያስፈርማል ብለዋል።

ቀበሌአችንን መገናኛ ብዙኃን አያውቁትም፤ ሃሣባችንን ተናግረን የፈለጉትን ቢያደርጉንም አንፈራም ሲሉ ማንነታቸውን ሳይደብቁ ከቪኦኤ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሁለት የቀበሌዪቱ ነዋሪዎች ቀደም ሲል ተወካዮቻቸውን ወደ ፌደራል መንግሥት ልከው እኛ ከዘር ማንዘራችን አማሮች ነን፤ ክልላችንም አማራ ክልል ነው ሲሉ ፊርማ አሰባስበው አቤቱታ ያስገቡትን ሰዎች ፖሊስ ጣቢያ እየጠሩ ያስፈራራሉ፤ ይዝታሉ ብለዋል።

“ሰዎች አሳስተውን ነው እያልን እንድፈርም እያደረጉን ነው፤ ነጭ ወረቀት ላይም እንፈርማለን” ብለዋል።

ስለሁኔታው የአካባቢው ባለሥልጣናት የሚሉትን ለመጠየቅ ወደ ሁመራ ወልቃይት ዞንና ወደ ወረዳው ያደረግናቸው በርካታ ጥረቶች ለጊዜው አልተሣኩም፤ በጥረታችን እንቀጥላለን።

በሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባይ ወልዱ የመሩት ስብሰባ እዚያው ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ ቆይቷል።

ስብሰባው የተወያየው በዚሁ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ላይ መሆኑም ተሰምቷል።

ከአራት የአካባቢው ወረዳዎች የተጠራ ወደ ስድስት መቶ የሚሆን ተሣታፊ ተገኝቶበታል።

የተሣታፊዎች የአቋም መግለጫ ነው የተባለ ሰነድም ወጥቷል።

የትግራይ ክልል የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊው አቶ ሃዱሽ ዘነበ “ይህንን ትርምስ የሚመሩት ኃይሎች ኢሕአዴግን በምርጫም በጦር ሜዳም ሊያሸንፉት ያልቻሉ ኃይሎች ናቸው፡፡ የሌለ የማንነት ጥያቄ እያነሱ እርስ በራሱ እንዲጫረስ፣ ከልማት ጎዳና ለማስወጣት እየሠሩ ይገኛሉ፤ ከሻዕቢያና ከሌሎች ኃይሎችም እነማን እንዳሉ መረዳት ይኖርብናል፡፡ መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ ትዕግሥቱ ተሟጥጧል” ብለዋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

መንግሥት ትዕግሥቱ ተሟጥጧል - የትግራይ የፀጥታ ኃላፊ
please wait

No media source currently available

0:00 0:14:39 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG