በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዋግ ኽምራ ዞን በተባባሰው ረኀብ የሰዎች እና የእንስሳት ሕይወት ማለፉ ተገለጸ


ፎቶ ፋይል፦ በዋግ ኽምራ ዞን ድርቅ
ፎቶ ፋይል፦ በዋግ ኽምራ ዞን ድርቅ

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በሰሀላ ሰየምት ወረዳ፣ በ2015/16 የምርት ዘመን የተከሠተው ድርቅ ያስከተለው ረኀብ ጉዳቱ በመባባሱ፣ ባለፈው ሳምንት በቢላዛ ቀበሌ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የቀበሌው አስተዳደር አስታውቋል፡፡

የድርቁ ኹኔታም እየከፋ መኾኑን ለአሜሪካ ድምፅ የገለጸው የወረዳ አስተዳደር፣ ተጨማሪ አምስት ሺሕ እንስሳትም መሞታቸውን አመልክቷል፡፡

በዋግ ኽምራ ዞን በተባባሰው ረኀብ የሰዎች እና የእንስሳት ሕይወት ማለፉ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:00 0:00

አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከ46ሺሕ በላይ ሰዎች በወረዳው መኖራቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ ለተጎጂዎች የርዳታ እህል የሚያጏጉዙ ተሽከርካሪዎች በጸጥታው ችግር ምክንያት ወደ አካባቢው ለመምጣት ፈቃደኛ አለመኾናቸው፣ እንዲሁም የተሰበረው የተከዜ ድልድይ አለመጠገኑ፣ ችግሩን አባብሶታል፤ ብለዋል፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ የመንገዱን ችግር እንዲከታተል ኃላፊነት እንደተሰጠው የጠቆሙት፣ የዐማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በበኩላቸው፣ ችግሩ ከተቀረፈ የርዳታ እህል ለመላክ ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በሰሃላ ሰየምት ወረዳ ቢላዛ ቀበሌ፣ በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን ከተከሠተው ድርቅ ጋራ በተያያዘ የቀጠለው የረኀብ ጉዳት፣ አሁንም ለሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት እየኾነ እንደሚገኝ፣ አስተዳዳሪው አቶ ማለደ ብሬ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው የመኸር ምርት ዘመን በዞኑ ያጋጠመው የዝናም እጥረት ባስከተለው ረኀብ፣ ስድስት ሰዎች እና ከ10ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን፣ የዞኑ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምሕረት መላክ፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ለአሜሪካ ድምፅ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በዞኑ በ26 ወረዳዎች ውስጥ የሚኖር ከ400ሺሕ በላይ ሕዝብ፣ አስቸኳይ የምግብ እህል ርዳታ እንደሚያስፈልገውና ከ1ነጥብ2 ሚሊዮን በላይ እንስሳትም የመኖ እጥረት እንዳለባቸው ኃላፊው በወቅቱ ሲገልጹ፣ በቂ ርዳታ ግን ወደ ዞኑ እየገባ እንዳልኾነም ተናግረዋል፡፡

የሰሃላ ሰየምት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ብሩ፣ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ እንዳስረዱት፣ ወረዳው ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ቢኖረውም፣ ከድርቁ ጉዳት የተነሣ ቁጥራቸው እየተመናመነ ይገኛል፡፡ በቅርቡም፣ በሺሕዎቹ የሚቆጠሩ ተጨማሪ እንስሳት መሞታቸውን፣ አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡

ለረኀቡ መባባስ፥ የርዳታ እህል የሚያጏጉዙ ተሽከርካሪዎች በጸጥታው ችግር ምክንያት ወደ አካባቢው ለመምጣት ፈቃደኛ አለመኾናቸው እንዲሁም የተሰበረው የተከዜ ድልድይ ተመልሶ አለመጠገኑ፣ ለረኀቡ መባባስ ምክንያቶች እንደኾኑ ዋና አስተዳዳሪ ጠቅሰዋል፡፡

የዐማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል፣ የርዳታ እህል እንዳልተላከ አምነው፣ ዕንቅፋት የኾነውም የተከዜ ድልድይ አለመጠገን ነው፤ ብለዋል፡፡ የዞኑ አስተዳደር የመንገዱን ችግር እንዲፈታ ትእዛዝ እንደተሰጠው ኮሚሽነሩ ጠቁመው፣ ችግሩ ከተፈታ የርዳታ እህል ለመላክ ዝግጁ እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን፣ ለዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኀይሉ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም፣ ስልኩ ባለመሥራቱ ምላሻቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ፣ ባለፈው ወር ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቸገሩ ዜጎችን ማግኘት በማይችሉበት ኹኔታ ተደራሽነቱ አስቸጋሪ መኾኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG