በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት የሚያታዩ የብሔር ብሔረሰብ ግጭቶችና ሌሎች ስምምነትና መግባባት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች እንዴት እንፍታ ሲሉ አንድ የማህበረሰብ ተቋምና የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ሊመካከሩ ቀጥሮ ይዘዋል።
የጋራ እንቅስቃሴ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የማህበረሰብ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰሜን አሜሪካና በተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሳል። የፊታችን ወር የፍቅር ቀን (Valentine’s Day) ሲከበር አንድ የማህበረሰብ የፍቅር ቀን ብለው የተለያዩ ሰዎችን አሰባስበው ስለአብሮነት ለመነጋገር አቅደዋል።
“ከጎሳ ይልቅ ለሕብረተሰባዊነት ቅድሚያ እንስጥ” ይላል የድርጅቱ መሪ ኦባንግ ሜቶ። በቅርቡ በአኝዋክና ኑዌሮች መካከል በጋምቤላ የተከሰተው ግጭት ለበርካታ ሰዎች ምክንያት ሆኗል። በኢትዮጵያ ሶማሊዎችና በቦረና ኦሮሞ፣ በአፋርና ኢሳ፣ በቅርቡ በጎንደር፣ በኦሮሚያና ሌሎችም አካባቢዎች የተቀሰቀሱና የሚቀሰቀሱ ግጭቶች በእጅጉ አሳስበውናል ይላሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭዎች።
ልዑል ፈቃዱ የ24 ዓመት ወጣት ነው። የተወለደው በኢትዮጵያ ሲሆና ከ10 ዓመቱ ጀመሮ ያደገው በዩናይትድ ስቴይትስ ነው። ልዑል በአሜሪካ የማንነት ፍለጋው የተለያዩ ቦታዎች እንደወሰደው፣ ኢትዮጵያዊነቱን ማወቁና ታሪኩን ማንበቡ እንደጠቀመውና፣ አንዳንዴ ደግሞ ግራ እንዳጋባውና አሁንም ብዙ መልስ የሚፈልግላቸው ጥያቄዎች እንዳሉት ያስረዳል።
“ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆኖ በአንድላይ የምንነጋገርባቸው መድረኮችን የግለሰብ ግንኙነቶች አስፈላጊ ናቸው” ይላል። ለዚህ ነው በበጎ ፈቃድ አገልጋይነት የማህበረሰብ ውይይት አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምነው። ሐሳቡ እንዲህ ነው። በአሁኑ ወቅት የሚከሰቱ ግጭቶችን በማህበርሰብ ውይይት እንዴት እንፍታ ሲሉ በዚህ በመጭው የካቲት ወር ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብለው ሊመክሩ ያሰቡት።
ከዚህ ምክክር የሚወጡ የጋራ ሐሳቦች፣ በተለያዩ ግለሰቦች አንደበት ለህዝብ ይፋ ሊሆን ታቅዷል። ማህበረሰባዊ እርቅ ለማምጣት ይረዳሉ ያሏቸውን ሐሳቦች የሚያካፍሉት ደግሞ በሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ በፍቅር ቀን (Valentine’s Day) እንደሚሆን ተናግረዋል።
ከዚህ በታች ያለውን የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።