በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ የጉዞ ማስጠንቀቂያውን አራዘመች


ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ላሰቡ አሜሪካውያን ዜጎቿ ቀደም ሲል አውጥታው የነበረውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ አራዝማለች፡፡የኢትዮጵያ መንግሥት “መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል"ብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጥቅምት 11/2009 ዓ.ም የወጣውን የሚተካ የጉዞ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ በመግለፅ ትናንት ባወጣው አዲስ የጉዞ ማስጠንቀቂያ በኢትዮጵያ በኅዳር 2008 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ፀረ-መንግሥት አመፅና አመፁን ተከተሎ የተፈጠረው የፀጥታ ሁኔታ ወዴት እንደሚያመራ መተንበይ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁሞ የአሜሪካ ኤምባሲ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ያለምንም ማስጠንቀቂያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሊቋረጥ እንደሚችል አመልክቷል፡፡በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል ወጥቶ የነበረው የጉዞ ማስጠንቀቂያ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ አገልግሎቶች በመላ ሃገሪቱ በየወቅቱ ያለማስጠንቀቂያ ስለሚቋረጡና ሙሉ በሙሉም ስለሚዘጉ ሁኔታው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎቹን የመርዳት አቅሙን እንደሚያደናቅፍ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ማስታወቂያ አብራርቷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች አማራጭ የግንኙነት ዘዴዎች እንዲኖሯቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖሩ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸውን እንዲያሳውቁ ማስታወቂያው መክሯል፡፡

መንግሥቱ ሰላማዊ ሠልፎችን ለመበተን ሰዎች ላይ በቀጥታ ሊተኩስ እንደሚችል፣ ሰላማዊ ሊሆኑ ለታሰቡና ለሚጠሩ ሰልፎች የኃይል ምላሽ እንደሚሰጥና ሰልፎቹ ያለማስጠንቀቂያ ወደ ሁከትነት ሊለወጡ እንደሚችሉ ዜጎቹ ማስታወስ እንደሚኖርባቸው የጠቆመው ይህ መልዕክት የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች የደኅንነት ሁኔታቸውን እየተከታተሉ አስፈላጊ ከሆነም ፈጥነው ከሃገር መውጣት የሚያስችላቸውን የአደጋ ጊዜ ዕቅዶች እንዲያዘጋጁ መክሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ነገሪ ሌንጮ ለቪኦኤ በሰጡት ምላሽ “መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል፤ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው ማስታወቂያ ግን የራሱ አቋም በመሆኑ ለአሜሪካ መንግሥት እንተወዋለን” ብለዋል፡፡

ጽዮን ግርማ ዝርዝር አላት።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

ዩናይትድ ስቴትስ የጉዞ ማስጠንቀቂያውን አራዘመች
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:25 0:00

XS
SM
MD
LG